“የደብረ ማርቆስ የአውሮፕላን ማረፊያ ፋይዳው ብዙ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

10

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ደብረ ማርቆስ ከተማ የጎጃም ክፍለ ሀገር መቀመጫ ኾና ለረጅም ጊዜ ያገለገለች ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱን ከሰሜን ምዕራብ ጋር ስታገናኝ የኖረች ናት ብለዋል።

በውስጧ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሃብቶችን ያቀፈች መኾኗንም ገልጸዋል። ከዓመታት በፊት የአየር መንገድ ተጠቃሚ የነበረች ቢኾንም በመካከል ተቋርጦ የሕዝብ ጥያቄ ኾኖ መኖሩን አንስተዋል።

ደብረ ማርቆስ የበርካታ ጸጋዎች ባለቤት እንደኾነች ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የደብረ ማርቆስ ከተማ ሕዝብ የአውሮፕላን ማረፊያ ጥያቄን ለዓመታት ሲጠይቅ ቆይቷል፤ ነገር ግን አይኾንም የሚል ተስፋ አስቆራጭ መልስ ይሰጠው እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ግን ያ ተስፋ ጥያቄ መልስ አግኝቶ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።

ከዓመታት በፊት አይኾንም የተባለው ተስፋ አስቆራጭ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ዛሬ የተመረቀው የአውሮፕላን ማረፊያ ፋይዳው ብዙ ነውም ብለዋል። የተጋመደች ኢትዮጵያን የበለጠ ለማስተሳሰር፣ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አንስተዋል።

አሁን የሕዝብ ጥያቄ ተመልሷል፤ ሌሎች ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ ተስፋ አለኝ፤ ነገር ግን የልማት ሥራዎችን ለማረጋገጥ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በአማራ ክልል በሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ አሜካላዎች አሉ፤ ሕዝባችን በስቃይ ውስጥ እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው፤ እነዚህን መታገል እና ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሕዝቡ አሜካላዎችን እንዲታገላቸው እና ሰላሙን እንዲያረጋግጥም አሳስበዋል።

የአውሮፕላን ማረፊያው ምርት እና ምርታማነትን እንድናሳድግ የሚያስገድድ ነው ብለዋል። ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ከሁሉም የሚጠበቅ መኾኑንም አንስተዋል። የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

#አሚኮ_ዜና #DebreMarkosAirport #ንጉሥተክለሃይማኖትአውሮፕላንማረፊያ #EthiopiaAviation

#ባሕር ዳር:ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“እየተግባባን መሥራት እና ማደግ ይገባናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በደብረ ማርቆስ ከተማ ችግኝ ተከሉ።