
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቀድሞዋ መንቆረር የአሁኗ ደብረ ማርቆስ የጎጃም ክፍለ ሀገር መናገሻ፣ የወሎ እና የወለጋ መገናኛ ድልድይ ኾና ስታገለግል እንደነበር ተናግረዋል።
መደመር መልካም መልካሙን ከፍ እያደረገ የሚሄድ መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፕላን ማረፊያው እውን እንዲኾን ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ደብረ ማርቆስ ከዓመታት በፊት የተሻሉ ከተባሉ 20 የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ተወዳድራ አሸንፋ ነበር፤ አሁን ግን በዚያ ልክ ናት ወይ የሚለውን መጠየቅ ይገባናል ብለዋል።
“አትመጣም ወይ ማርቆስ ከንጉሥ ከተማ ቢያሻህ በአውሮፕላን ቢያሻህ በሎንችና” ተብሎ የተገጠመላት ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውሮፕላኑ ተመልሷል ሎንቺናውንም በእኛ ጊዜ መመለስ አለብን ነው ያሉት።
በአካባቢው እምቅ ጸጋ አለ፤ ይሄን የመሰለ ሃብት ይዘን መከፋፈል፣ መጋጨት አያስፈልገንም ብለዋል። እየተግባባን መሥራት እና ማደግ ይገባናልም ነው ያሉት። ደብረ ማርቆስ የሕዝቦች መገናኛ ድልድይ ኾና ዕድገት ስታሳልጥ የኖረች ናት፤ አሁን ላይ ዓባይ አካባቢ መሽገው ሰዎችን የሚያሰቃዩ ሽፍቶች እንዳሉም ተናግረዋል። ከደብረ ማርቆስ ደጀን ድረስ ሰዎች እንደፈለጋቸው እንዳይሄዱ የሚያደርጉ ሽፍቶችን ማስወጣትም ያስፈልጋ ብለዋል።
ግጭት እና መከፋፈል አስፈላጊ አይደለም፤ በጋራ ኾኖ ሰላምን ማረጋገጥ እና ልማትን ማፋጠን ነው የሚጠቅመው፤ ከዚያ ውጭ ያለው አካሄድ ሕዝብን ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም ነው ያሉት።
መንግሥት የሰላም አማራጭን ለሚፈልጉ ኀይሎች ሁሉ በሩ ክፍት ነው፣ እጁም ለሰላም የተዘረጋ ነው፤ እንወያይ፣ ሰላምን እናረጋግጥ፤ ከዚያ ውጭ ያለው አካሄድ ኢትዮጵያን አይጠቅምም ብለዋል። ውጊያ ሞት እና ኪሣራ እንጂ ጥቅም እንዳልተገኘበትም ተናግረዋል።
በተባበረ እና በተደመረ ክንድ ሀገርን ማልማት እንደሚገባም ገልጸዋል። ልማት በአንድ ጀንበር የሚሠራ አይደለም ትዕግሥት እና ጊዜ ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ለሚመልሰው ጉዳይ መገዳደል እንደማያስፈልግ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ትልቅ ባለጸጋ ናት የጎደላት መወያየት እና መልማት ነውም ብለዋል።
የአውሮፕላን ግንባታው በመጠናቀቁ እንኳን ደስ ያላችሁም ነው ያሉት። ደስታችሁን በመጋራቴም ደስ ብሎኛል ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #DebreMarkosAirport #ንጉሥተክለሃይማኖትአውሮፕላንማረፊያ #EthiopiaAviation
#ባሕር ዳር:ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
