🚀 የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ሽግግር የት ላይ ነው?

6

 

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በዲጂታላይዜሽን ዘርፉ ከፍተኛ መዋቅራዊ እና ተግባራዊ ለውጦችን አስመዝግባለች። በተለይም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ይፋ መደረጉ ለዚህ ለውጥ ትልቅ አጋዥ እንደኾነ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ከለውጦች መካከል 📞የኢትዮቴሌኮም ዘርፍ አንዱ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን መረጃ የኢትዮቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ይዞታነት መዞር እና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ገበያ መግባት የኢንተርኔት ተደራሽነትን እና ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሏል። የ4G እና 5G ኔቶርኮች መስፋፋትም የዚሁ ውጤቶች ናቸው።

የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትም ሌላው ለውጥ እንደኾነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያስረዳል።📱የቴሌብር አገልግሎት መጀመር እና የሞባይል ባክኪንግን ጨምሮ ባንኮች የዲጂታል መተግበሪያዎች መስፋፋት የገንዘብ ዝውውርን አቅልለዋል። ይህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ መደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት አስገብቷል። የብዙዎችን እንግልትም ቀንሷል። ቀልጣፋ የገንዘብ ልውውጥ እንዲኖርም አድርጓል።

💻 የመንግሥት አገልግሎቶች ዲጂታላይዜሽንም ሌላው ተግባር ነው። እንደ ፓስፖርት፤ የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ፤ የትራፊክ ቅጣት ክፍያ፤ የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ምዝገባ እና ሌሎችም አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል መሸጋገራቸው ቢሮክራሲን እና እንግልትን በመቀነስ ለውጦችን ያመጡ አሠራሮች ናቸው።

🚗 የትራንስፖርት ዘርፉም በአጋዥ መተግበሪያዎች በመታገዙ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ እያገዘ ነው። በኢኮሜርስ ዘርፍም በርካታ የሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተፈጥረዋል። እነዚህ በአብነት የተነሱ ለውጥ የታየባቸው ዘርፎች እና ሌሎችም ለቀጣይ ብዙ ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው። የኢኮሜርስ እና ዲጂታል ንግድ በማደጉ የዲጂታል ክፍያ እና የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ እየተቀናጀ በመምጣቱ የኦንላይን ግብይት በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የመኾን ተስፋ አለው።

💼 ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም የቴክኖሎጂ ዘርፉ መነቃቃት ለብዙ ሺህ ወጣቶች በሶፍትዌር ልማት፤ በዲጂታል ማርኬቲንግ እና በደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እየፈጠረ ይገኛል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድም ብዙ ተስፋ የሚጣልበት እየኾነ ነው። የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ተከትሎ የዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና የዳታ ማዕከላት ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ፍላጎትም እየጨመረ ነው።

በጥቅሉ የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ባለፉት ዓመታት አስደናቂ እምርታ አሳይቷል። እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ማኅበረሰብ ሰፊ ለውጦች ታይተዋል። ይሁን እንጂ የተጀመሩ ስኬቶች ዘላቂ እንዲኾኑ የሳይበር ደኅንነትን ማጠናከር፤ የመብራት እና የኢንተርኔት መሠረተ ልማትን አስተማማኝ ማድረግ እና በገጠርና በከተማ መካከል ያለውን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ልዩነት ማጥበብ በቀጣዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው።

#ሐምሌ04/2018#አሚኮ
#Ethiopia🇪🇹 #DigitalEthiopia2025 #Technology #DigitalEconomy #Telecom #CyberSecurity
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ3_2018_ዓ_ም

✍️ በሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየቀይ ባሕር ባለግርማ ኢትዮጵያ 🇪🇹🚢
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የልማት ሥራዎችን ለመመረቅ ደብረ ማርቆስ ከተማ ገቡ።