
ኢትዮጵያ በየዘመናት በተለያዩ ኃይሎች ተፈትናለች። ውስጣዊ እና ውጫዊ ኃይሎች በሉዓላዊነቷ ላይ አያሌ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለያየ ወቅት ጥምረት እየፈጠሩ ከውስጥ ወግተዋታል፤ ለውጭ ታሪካዊ ጠላቶችም አሳልፈው ሰጥተዋታል።
ኢትዮጵያ ተጽዕኖዎችን እየተቋቋመች፤ ፈተናዎችን በአሸናፊነት እየተወጣች፤ ጠላቶቿን ድል እያደረገች ለዛሬው ትውልድ ደርሳለች። ሁሉንም አይነት ሙከራዎችን እያከሸፈች ዘልቃለች።
ከአጼ ኃይለ ሥላሴ እስከ ደርግ ድረስ መንግሥትን በኃይል ለመቆጣጠር የተመሰረቱት ኦነግ፣ ሻቢያ እና ሌሎችም የግራ ዘመም ፓለቲካ አራማጅ ድርጅቶች ከግብጽ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አብረው ሠርተው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።
አሁን ያለውን መንግሥት በኃይል በመተካት እና ኢትዮጵያን በመበታተን የሥልጣን ጥማቸውን ለማርካት እና ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚቋምጡ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች “ጽምዶ” የሚል ጥምረት መፍጠራቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
በዚህ የፖለቲካ ትወና በተለይም የሀገር ክህደት የፈጸመው የሕወሃት ቡድን የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ይህ ተገቢ ያልኾነ አካሄድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናም የሰላም ጠንቅ ስለመኾኑም ካለፉት ዓመታት ታሪክ የታየ ነው።
በአማራ ክልል በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ትብብር በ2014 ዓ.ም በታተመው መጽሐፍ ላይ “የሕወሃት ቡድን በሁለንተናዊ ማንነቱ በክህደት ያደገ ምንም አይነት ሕግ፣ ሞራል፣ ፖለቲካ እና መርህ አይዳኘውም” ሲል ያትታል።
የሕወሃት ክህደት በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ከአንቀጽ 238 እስከ 260 የተደነገጉትን “በሀገር እና ሕዝብ ላይ የሚፈጸም በመንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ በሀገር መከላከያ ኃይል፣ በኢኮኖሚ፣ በስለላ፣ ከጠላት ጋር በመተባበር፣ እና ሌሎችንም ከፍተኛ የክህደት ወንጀሎች የፈጸመ ቡድን ስለመኾኑም በመጽሐፉ ተጠቅሷል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጽምዶ አሁን የተፈጠረ ሳይኾን በ1960ዎቹ ጀምሮ የነበረ የጠላት ከንቱ ሕልም መኾኑን ይገልጻሉ።
ይህም በወቅቱ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ፤ ዓባይን እንዳትገድብ፤ በቀጣናው ደካማ ሀገር እንድትኾን ሢሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። በወቅቱ የነበሩት ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር ተቀናጅተው ዛሬም እንደገና መጥተዋል ነው ያሉት።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ጽምዶ የጸረ ሉዓላዊነት እሳቤ ያለው እና የቅዠት አስተሳሰብ ተሸካሚዎች ጥምረት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለ”ጽምዶ” አስተሳሰብ ተሸካሚዎች እና አሥፈጻሚዎች ቦታ እንደሌላት የሚናገሩት ጄኔራሉ በእነዚህ ኃይሎች ለሚፈጥሩት ትንኮሳ እንደማትታገስም አስጠንቅቀዋል።
“ጽምዶ” በሚል ስብስብ የፈርዖንን ቀንበር ተሸክመው ኢትዮጵያን ለመውጋት የሚመጡ ኃይሎች ቢኖሩ እንኳን እንደሰም ይቀልጣሉ ብለዋል።🔥🕯️
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት ሕወሃት እና ሌሎች የውስጥ ኃይሎች የውጭ ኃይሎች ዓላማ ፈጻሚ ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ኃይሎች ለሚልካቸው አካላት መጠቀሚያ ከመኾን ውጭ የሚፈይድላቸው ነገር እንደሌለም አስገንዝበዋል። ከላኪወቻቸው ይልቅ የኢትዮጵያ እድገት እና ሰላም ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው መክረዋል።
ለኢትዮጵያ ሰላም መደፍረስ ምክንያቱን ከምንጩ እናውቀዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ላይ ለሚደረግን ማንኛውንም ትንኮሳ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩን አረጋግጠዋል።
#የኢትዮጵያ_ሉዓላዊነት / #EthiopianSovereignty
#ጽምዶ / #Tsimdo
#የሀገር_መከላከያ_ሰራዊት / #ENDF
#ሐምሌ02_2018_ዓ_ም
በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
