በምግብ ራስን መቻል ነጻነት እና ክብር ነው።

3

 

ኢትዮጵያ የልምላሜ እና የብዝኃ-ሕይወት ማማ፣ የውኃ ማጠራቀሚያ፣ የጥበብ እና የረጅም ዘመን የግብርና ሥራ ታሪክ ባለቤት ሀገር ናት። ዛሬ ይህች ታላቅ ሀገር የለመነችውን ሳይኾን የለፋችበትን፤ የተመጸወተችውን ሳይኾን ያመረተችውን ለመመገብ በጽኑ ቁርጠኝነት እና በልዩ ወኔ እየተጓዘች ትገኛለች።

ይህ ጉዞ በደም እና በአጥንት ተከብሮ እና ተጠብቆ የኖረውን ነጻነታችንን በማስጠበቅ፤ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ፤ የብሔራዊ ክብር እና የማንነት መገለጫ የኾነ አዲስ የነጻነት ምዕራፍ ነው።

የሀገሪቱ በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ በባዶ መፈክር ሳይኾን በላብ፣ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ታሪካዊ የልማት አብዮት ነው። ትናንት በስንዴ እርዳታ እና በረሃብ ታሪክ የምትታወቀው ሀገር ዛሬ በፈሰሰላት የንጋት መስኖ ልማት፣ በደማቅ የክረምት እና የበጋ የልማት ሥራዎች እሸት አምራች እና ለውጭ ገበያ የምታቀርብ እምቅ እና ተጨባጭ አቅም ያላት ኾናለች።

ከሰፋፊ እርሻዎች ባሻገር በየመኖሪያ ቤቱ የሚንጸባረቀው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ የእንስሳት፣ የዶሮ፣ የንብ እና የዓሣ እርባታን ቷ፣ የጓሮ አትክልት ልማትን በማነቃቃት የንጥረ-ነገር (የአልሚ ምግብ) ዋስትናን እያደሰ እና ማኅበረሰባዊ ጤናን እየጠበቀ ነው።

በዚህ ሀገራዊ የድል ጉዞ ውስጥ የአማራ ክልል ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ እና የግብርና ዐውደ ምሰሶ ኾኖ በልዩ ግርማ ቆሟል። የክልሉ ተፈጥሯዊ ጸጋ እና የታታሪው ሕዝብ የማይበገር ማንነት ተዳምረው በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ ላይ ግዙፍ እና አስተማማኝ አቅም ፈጥረዋል።

የሰብል ልማት ማማ የኾኑት የክልሉ አካባቢዎች የበቆሎ፣ የስንዴ እና የጤፍ ጎተራነታቸውን በተግባር እያስመሰከሩ ነው። በክረምት በአረንጓዴ ምንጣፍ የሚለብሱት ሰፊ ሜዳዎች፣ በበጋ ደግሞ በወርቃማ ሰብል ተሞልተው ሲታዩ ልብን በሐሴት እና በኩራት ይሞላሉ።

በወጣ ገባ እና ውብ መልክዓ-ምድሮች ውስጥ የሚገኙ ጀግና አርሶ አደሮች ተራራውን እየተከተሉ፣ ምንጮችን እየጠለፉ የፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች እና የአትክልት ምርትን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደጉ ይገኛሉ። የውኃ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ የማምረት አዲስ የግብርና ባሕል እና ልማድ በስፋት እየሰረጸ መጥቷል።

ለውጡን ተከትሎ የሀገራችን የብልጽግና ማሳያ ምስክር የኾነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተቀርጾ፣ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሁለንተናዊ ጥቅም ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል፤ እየተተከሉም ይገኛሉ። ይህ ዓለም ያወቀውና ያደነቀው ውብ የሰው ልጆች አሻራ ወጣቶችን፣ የጸጥታ ኃይሎችን፣ አረጋውያንን ፣ ፖለቲከኞችን እና የሃይማኖት አባቶችን ያሳተፈ የአንድነት ተምሳሌት የኾነ ተግባር ነው።

ከችግኝ ተከላው ባለፈም እንደ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ቡና እና መሰል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ያላቸው የእፅዋት ዝርያዎች በሰፊው ተተክለዋል። ይህም አይቀሬውን የብልጽግና ጉዞ በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ከጣና ሐይቅ ዳርቻ እስከ ተከዜ እና አንገረብ ተፋሰስ፣ ከሰሊጥ (ነጩ ወርቅ) እና ቀይ ጤፍ እሸት እስከ ነጭ ስንዴ አዝመራ ድረስ ክልሉ የኢትዮጵያን የውስጥ ፍላጎት በልዩ ሁኔታ ከመሸፈን አልፎ፣ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚተርፍ ታላቅ እምቅ አቅም እንዳለው ተግባራዊ እመርታ እያሳየ ነው።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ይህ ታላቅ ንቅናቄ ረሃብን እና ጥገኝነትን የታሪክ ዕዳ አድርጎ ለመቅበር የሚደረግ የትውልድ ዘመቻ ነው። አርሶ አደሮች በማለዳ ወጥተው ማሳቸውን ሲያርሱ እና ሲያለሰልሱ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ምርጥ ዘር ከባሕላዊው ጥበብ ጋር ሲዋሃዱ፤ ኢትዮጵያ እና የአማራ ክልል የራሳቸውን የነገ ብሩህ ተስፋ በገዛ እጃቸው እየጻፉ መኾናቸውን ያበስራል።

በምግብ ራስን መቻል ማለት ፍጹም ነጻነት እና ክብር ነው፤ ይህ ጉዞ ደግሞ የኢትዮጵያ እውነተኛ የትንሣኤ እና የብልጽግና ጉዞ ነው፡፡ ድህነትን እና ኋላቀርነትን ታሪክ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እና ርብርብ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አወንታዊ ድርሻውን እንዲወጣ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል።

#በምግብ_ራስን_መቻል #የኢትዮጵያ_ብልጽግና #የሉዓላዊነት_ማረጋገጫ

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ03_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከታሪካዊ ጠላቶች እስከ ውስጣዊ ባንዳዎች፤ የጽምዶ ሴራ እና የኢትዮጵያ ዝግጁነት