
ዝክረ ሐምሌ አምስት 2008 ዓ.ም አሥረኛ ዓመት በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሰቲት ሁመራ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
ቀኑ ሕወሃት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሠብሣቢውን ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ከጎንደር አፍኖ ለመውሰድ ሙከራ ያደረገበት እና የሽንፈቱ መጀመሪያ የተረጋገጠበት ቀን ነው።
ሐምሌ አምስት 2008 ዓ.ም ለሀገራዊ ለውጡ እርሾ የተጣለበት ቀን መኾኑን ያመላከቱት በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው።
ሕወሃት ለዘመናት የገነባው የአማራ ሕዝብ የጨቋኝ ተጨቋኝ የተዛባ ትርክት የተሻረበት እና የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብም የነጻነቱ ወጋገን የታየበት መኾኑን አመላክተዋል።
በብዙ መስዋዕትነት ዛሬ ላይ የተገኘውን ነጻነት አጠናክሮ መቀጠል የዚህ ትወልድ አደራ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ነጻነትን በጋራ ዳር ማድረስ ቁልፍ ጉዳይ መኾኑንም አስረድተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ እና መላው የአማራ ሕዝብ በወቅቱ በተደረገው መራር ትግል ዛሬ ላይ ነጻነቱን መጎናጸፉን የገለጹት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሠብሣቢ እና የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው።
የሐምሌ አምስት 2008 ዓ.ም ትግል የአንድነት ኃይል የታየበት መኾኑንም አንስተዋል። ዛሬ ላይ በቋንቋ፣ በዘር እና በብሔር ባለመገፋፋት አንድነትን አጠናክሮ በሰላም ለመኖር ሁሉም ዝግጁ ሊኾን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ሐምሌ አምስት ነጻነትን ሲናፍቅ እና በቁርጠኝነት ሲታገል ለነበረው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ታላቅ ቀን ነው ብለዋል። ይህ ቀን የመላው አማራ እና ኢትዮጵያዊ ኩራት፤ የዞኑ ሕዝብ ነጻነቱን እንዲጎናጸፍም ብዙ የሕይወት ዋጋ የተከፈለበት መኾኑን ነው የተናገሩት።
የነጻነት ትግል በጥቅም የማይለወጥ ታላቅ ዓላማ መኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ ወጣቱ ትውልድ የዚህን ትግል ዓላማ ከግብ ለማድረስ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት አመላክተዋል።
መሪዎች ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
#የወልቃይት_ጠገዴ_ሰቲት_ሁመራ #አማራ_ማንነት #የነጻነት_ቀን #አሚኮ #AMHARA #Ethiopia
#ሁመራ_#ሐምሌ02_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
