
ኢትዮጵያ በታሪኳ ካጋጠሟት ውሥብሥብ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ቀውሶች ለመውጣት አዲስ የመፍትሔ በር አንኳኩታለች። እሱም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው። ይህ ኮሚሽን ለዘመናት የዘለቁ የሀሳብ ልዩነቶችን፣ የታሪክ ቁስሎችን እና የፖለቲካ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የተቋቋመ ትልቅ ሀገራዊ ተስፋ ነው።
በግጭት እና በሰላም እጦት የደከመው ሕዝብ በዚህ ምክክር ላይ ያለው ተስፋ እጅግ ከፍተኛ ነው። እናቶች ልጆቻቸው ከስጋት ነፃ ኾነው የሚኖሩባትን ሀገር ያልማሉ። የበደል ሰለባዎች ድምፃቸው የሚሰማበት የፍትሕ መድረክ አድርገው ከወዲሁ ያዩታል። ማኅበረሰቡ ለፖለቲካው መረጋጋት መፍትሔ እንደሚኾን ያምናል።
ይህ የሕዝቡ ተስፋ ለኮሚሽኑ ትልቅ የሕዝብ ድጋፍ አስገኝቶለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉንም ችግር በአንድ ጀምበር እንዲፈታ የሚጠብቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚኖሩ ሲታሰብ ከባድ የቤት ሥራ ይኾናል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች ኮሚሽኑ እስከታች ወርዶ በነፃነት መረጃዎችን ለመሠብሠብ እና የሕዝብ ድምጽ ለመስማት እንቅፋት ኾነውበት ነበር። ከሀገሪቱ ስፋት እና ከችግሮቹ ስር መስደድ አንጻር ሂደቱ ትዕግሥት የሚጠይቅ ነበር። በትዕግሥት እና በቁርጠኝነት ግን ፈተናዎችን ተሻግሯል፤ አካታችነትን እና አሳታፊነትን መርሑ አድርጎ ሠርቷል።
ኮሚሽኑ ወደ መፍትሔ የሚወስድ ድልድይ ነው። እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ተቋቁሞ እና ውጣ ውረዶችን አልፎ አብረውት ለዘለቁት ኢትዮጵያውያን የልፋቱን ፍሬ እንካችሁ ለማለት አሁን በዋዜማ ላይ ይገኛል።
የነገዋ ኢትዮጵያ ውበት ዛሬ በጠረጴዛ ዙሪያ በምናሳየው መደማመጥ እና መቻቻል ላይ የተመሠረተ ነው። ለዚህም ሀገራዊ ምክክሩን በፍጹም የጋራ ተጠቃሚነት እሳቤ እና ኀላፊነት አኳያ ማከናወን ከእያንዳንዱ ይጠበቃል።
ሀገራዊ ምክክር ብዙ ፋይዳዎች አሉት። የፖለቲካ ችግሮችን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ እና ለሀገር ሕልውና አስጊ የኾኑ ልዩነቶችን ለመፍታት መሠረት የሚጥል ነው።
ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት፤ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመንን የሚጠናከርበት፤ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከር እና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባሕል እንዲዳብር ያደርጋል።
ያደገና የተለወጠ ሥርዓት ባለቤት ለመኾን እና በዜጎች መካከል የተሻሻለ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ፋይዳ አለው።
በሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
