“ፍቱን መድኃኒቱ ምክክር ብቻ ነው”

4
ውይይት እና ምክክር የኢትዮጵያ ነባር እሴት ነው። በተለይ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፤ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና የሀገርን ሰላም እና አንድነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። ሽምግልና፣ ገዳ፣ ጆካ ምክር ቤት፣ ሉዋ፣ አበጋር እና ሺንጋ እየተባሉ የሚዘረዘሩት ባሕላዊ ሥርዓቶች በሁሉም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዘንድ በተለያዩ አግባቦች መገለጣቸው እንደ ሀገር ለውይይት እና ምክክር የምንሰጠውን ትልቅ ቦታ ማሳያ ነው።
ባሕላዊ ሥርዓቶቹ ማናቸውንም ትላልቅ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲሁም በግለሰቦች እና ማኅበረሰቦች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን በጠረንጴዛ ዙሪያ በመመካከር መፍትሔ ይሰጣሉ። የመወያየት እና የመመካከር ልምዱ አሁንም በባሕላዊ የእርቅ እና የዳኝነት ሥርዓት አማካኝነት ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታቸው ቀጥሏል።
ዘመናዊ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥራ ሲጀመርም አጋዥ በመኾን ለዴሞክራሲ ልምምድ እርሾ መኾንም ችለዋል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ለዘመናት ትኩረት ሳይሰጣቸው የቆዩ እና በጊዜ ሂደት እየሰፉ እና እየተካረሩ የመጡ ማኅበረ-ፖለቲካዊ አለመግባባቶች ለሀገር አደጋ መኾናቸው አልቀረም።
እነዚህ ልዩነቶች ተዋናያቸው እየበዛ የቆየውን የውይይት እና የምክክር ባሕል ሸርሽረው ጽንፈኝነት፣ ጥላቻ እና መገፋፋትን ሲተኩ ታይተዋል። ኢትዮጵያን ግጭት እና ጦርነት ውስጥ ዘፍቀዋታል።
የግጭት እና የጦርነት መንስኤ የኾኑ መሠረታዊ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ተቃርኖዎችን ከሕዝቡ አንደበት በመለየት ሕዝቡ ራሱ ተወያይቶ እንዲያስታርቃቸው ከባሕላዊ ሥርዓቶች የተቀዳ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል።
ኮሚሽኑ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ አካላትን ያሳተፈ የአጀንዳ ማሰባሰብ፤ የተሳታፊ ልየታ እና መድረክ የማዘጋጀት ሥራዎችን አከናውኗል።
በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 30ኛ መደበኛ ስብሰባም የግጭት እና የጦርነት አዙሪቶች በሐቀኛ ውይይት እና ምክክር ዘላቂ መፍትሔ ይሰጣቸው የሚለው ጉዳይ ተንጸባርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በትናንትነው እለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ በኢትዮጵያ ታፍነው የኖሩ ብዙ ጉዳዮች አሉ ብለዋል። ታፍነው የቆዩ ሀሳብች ዘመን ሲመቻቸው፤ መንግሥት የተሻለ መፈናፈኛ ሲሰጣቸው ይወጣሉ ነው ያሉት። መንግሥትም በተለያዩ አመክንዮዎች በትዕግስት ለማስተናገድ መሞከሩን አንስተዋል።
በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በድፍን ኢትዮጵያ ጨምሮ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ስለጉዳያቸው የሚወያዩበት መድረክ መፈጠሩን የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
በዚህም የማኅበረሰብ ግጭቶች ቀንሰዋል፤ ውይይት እና ምክክር ሲቀጥል ነገሮች እየሰከኑ ይሄዳሉ ነው ያሉት።
ታፍነው የቆዩ ችግርችን ለመቅረፍ ብሔራዊ ምክክሩ ሰፊ ዕድል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙዎች ለረጅም ጊዜ የጠየቁት፣ የታሰሩበት እና ዋጋ የከፈሉበት ስለኾነ ዕድሉ ሲገኝ ማቅለል ጥሩ አይደለም ብለዋል።
ይህ ውይይት ከታች ከሕዝቡ ጀምሮ የተደረገ ውይይት ስለኾነ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካውያንም ጠቃሚ እንደኾነ ገልጸዋል።
እኛ እንወያይ፣ እንመካከር፣ እንፍታ እያልን ያለነው ችግር እኛ የፈጠርነው አይደለም ብለዋል። የወሰን እና የማንነትም ኾነ የተጓተቱ ልማቶችን እኛ አልፈጠርናቸውም፤ እንፍታው የሚለውን ቁርጠኝነት ችግሩን እኛ እንደፈጠርን ተደርጎ መታየት የለበትም ነው ያሉት።
አሁን ያለው ትውልድ መክሮ እና ዘክሮ መፍታት አለበት የሚለውን እኛም እናምናለን ያሉት ዶክተር ዐቢይ ውይይቱን እየደገፍን ያለነውም ለዚያ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
በአድኖ ማርቆስ
#ምስል ከአርካይቭ
Previous article“ባለሀብቱን እና ኅብረተሰቡን በማሳተፍ የልማት ሥራዎችን ማፋጠን ይገባል” ሙሉነሽ ደሴ ( ዶ.ር)
Next articleከሽፋን ወደ ጥራት፤ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ አዲስ ጉዞ !