“45 በመቶ የሚኾነው የመድኃኒት አቅርቦት የሚመረተው በሀገር ውስጥ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

9

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ሥብሠባ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በ2018 በጀት ዓመት መንግሥት ለመድኃኒት ግዥ 70 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን አንስተዋል። በሀገር ውስጥ የነበረው መድኃኒት የማምረት አቅም 4 በመቶ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ 45 በመቶ እንዲያድግ ተደርጓል ነው ያሉት።

ፎሮኖስቲካል ላይ በተገባው ቃል መሠረት አሃሪ ላበራቶሪን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። ብዙ የሕክምና መሣሪያዎች እያስገባን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2018 በጀት ዓመት ለሕክምና መሣሪያዎች ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ መውጣቱንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ በሁለት እና ሦሥት ሆስፒታል የኢትዮጵያን ፍላጎት ማሟላት አይቻልም ነው ያሉት። አዲስ አበባ ውስጥ በጥቂት ወራት ብዙ አስመርቀናል ብለዋል። በሚቀጥሉት ወራት የሚመረቁ ሆስፒታሎች እንዳሉም ለምክር ቤቱ አባላት አስታውቀዋል።

ፎሮኖስቲካል እና ሆስፒታል ግንባታ ላይ በነበረው የመንግሥት የመቆጣጠር አቅም ምክንያት የዓለም የመድኃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ ኢትዮጵያን ማቹሪቲ ሌቭሊ ሦሥት እንዳላት ተናግረዋል።

ይህ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ያሉበት ደረጃ ነው ብለዋል። ትልቁ ማቹሪቲ ደረጃ አራት መኾኑንም ገልጸዋል። ይህ የሚያሳየውም ኢትዮጵያ የምታመርታቸው መድኃኒቶች ለኤክስፖርት ደረጃ ተቀባይነት አላቸው ማለት ነው ብለዋል።

ጤናው ዘርፍ ላይ እድገት አለ፤ ለውጥ አለ፤ ብዙ ደግሞ የሚቀር ነገር አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አበክረን በመሥራት የተሟላ ለውጥ እናመጣለን ብለዋል።

ከሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ሥራችን አንዱ በውጭ ሀገር ደረጃ የሚታዩ ጸዳ ያሉ የሕክምና መስጫ ተቋማት መገንባት ይኾናል ነው ያሉት።

ወባን ለመከላከል 14 ሚሊዮን አጎበር በነጻ ተሠራጭቷል፤ ሦሥት ሚሊዮን የሚደርስ ቤት ጸረ ወባ መድኃኒት ተረጭቷል ብለዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በ58 ወረዳዎች ክትባት መሰጠቱንም ጠቅሰዋል።

#የሕዝብ_ተወካዮች_ምክር_ቤት #የጤና_መሰረተ_ልማት #አሚኮ #Ethiopia #HealthSector #PMAbiyAhmed #HealthcareDevelopment
#ባሕርዳር_ሰኔ30_2018_ዓ_ም

በአድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሃይማኖት የሰላም መሰረት እንጂ የግጭት መሸሸጊያ ሊኾን አይገባም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የውጭ ግንኙነታችን የኢትዮጵያን የውሳኔ ሉዓላዊነት ማስጠበቅ መሠረት ያደረገ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)