
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ሥብሠባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር አቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ በብዝኀ እምነቶች የተዋበች ሀገር ናት። ሃይማኖቶች የሰላም መሠረት እንጂ የጥል መነሻ ሊኾኑ አይገባም ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት በአብሮነት የኖረ በመኾኑ ይህንን ታላቅ እሴት ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል።
በተለይም ክርስትና እና እስልምና አብሮ ተደጋግፎ የኖረ እንደኾነ ጠቁመዋል። በሃይማኖት ሽፋን ምርጫን ለማደናቀፍ የተደረገ ዝግጅት እንደነበረም አስታውሰዋል። አርሲ አካባቢ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የሃይማኖት ሳይኾን የነበረውን ሰላም ለማደፍረስ የተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም የጸጥታ አካላት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል የንፁሃንን ደኅንነት ታድገዋል ነው ያሉት። ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል። በርካታ ጉዳዩን ያባባሱ አካላትም እንደተያዙ ጠቁመዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎች ከ90 በመቶ በላይ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንም ገልጸዋል። ሌሎችን ለመመለስ እየተሠራ ይገኛልም ነው ያሉት።
በሃይማኖት እና በብሔር ስም ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሰላም የሁላችንም የጋራ ኀላፊነት በመኾኑ ሃይማኖትን የግጭት መሸሸጊያ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባም አመላክተዋል።
#አሚኮ_ዜና #የምክር_ቤት_ውሎ #PMAbiyAhmed #Parliament
በሥራውድንቅ ደሳለው
#ባሕር_ዳር_ሰኔ_30_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ
