
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በትምህርት ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉ ሀገራዊ ሥራዎች ዙሪያ ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ማብራሪያቸውም መንግሥት የነገዋን ኢትዮጵያ ለሚረከቡ ታዳጊዎች ትኩረት በመስጠት በትምህርት መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በዝርዝር አስገንዝበዋል።
በተለይም የትምህርት ተቋማትን ለማስፋፋት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በሁሉም ክልሎች የሞዴል እና አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል።
በግጭት ምክንያት የተበላሹ፤ የተቃጠሉ እና የፈራረሱ በርካታ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመጠገን ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የመሰረተ ልማት ግንባታው ጥራቱን የጠበቀ እንዲኾን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት። አሁን እየተገነቡ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ደረጃን ያሟሉ እና የተሻሉ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ 35 ሺህ መዋለ ሕጻናት መገንባታቸውን ጠቁመዋል። ይህ ትልቅ ኢንቨስትመንት ለአጭር ጊዜ ሳይኾን ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ታዳጊዎች ህልውና ታሳቢ ተደርጎ የተሠራ ነው ብለዋል። የነገዋን ኢትዮጵያ የሚገነባው የትምህርት ኢንቨስትመንት እንደኾነ ነው የገለጹት።
ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ እና ከመሳሰሉ የገቢ ምንጮች በተገኘው ሀብት ብቻ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች 35 ሞዴል ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።
በዘርፉ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት መምህራን ተማሪዎቻቸውን ብቁ አድርገው ለማሳለፍ ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ስምምነት ያለ ቢሆንም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የነበረውን ስብራት ሙሉ በሙሉ አድሶ እና መምህራንን በበቂ ሁኔታ አዘጋጅቶ የተሟላ ውጤት ለማየት ግን የተወሰነ ጊዜ እንደሚወስድ ጠቁመዋል።
#ኢትዮጵያ #ትምህርት #መሰረተ_ልማት #የህዝብ_ተወካዮች_ምክር_ቤት #ዐቢይ_አሕመድ #Education #PMAbiyAhmed #Development #EthiopianEducation
በስማቸው አጥናፍ
#ባሕርዳር_ሰኔ30_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
