ለምክር ቤቱ የሚቀርቡ የአሥተዳደር ወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ቁጥር መቀነሱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።

5
የፌዴሬሽን ምከርቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
ምክር ቤቱ በጉባኤው ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል የማንነት፣ የአሥተዳደር ወሰን እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አንደኛው ነው።
✍️ በጉባኤው ላይ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች፡-
👉 የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች መቀነስ፦
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለክልሎች በተደረገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እና ክትትል ምክንያት ግጭቶች እንዳይፈጠሩ እና የማንነት ጥያቄዎች በዚያው በአጭሩ እንዲፈቱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የተነሳ “ወረዳ ልሁን፣ ዞን ልሁን” የሚሉ የማንነት ይታወቅልኝ እና የአሥተዳደር ወሰን ጥያቄዎች አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን ገልጸዋል።
👉 የብሔረሰቦች አትላስ ጥናት እጥረት፦
የማንነት፣ የአሥተዳደር ወሰን እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ፍቅሬ አማን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የማንነት መገለጫ አትላስ ለማጥናት የምክክር መድረኮች ቢካሄዱም በበጀት እጥረት ምክንያት የጥናት ሥራውን በአግባቡ ማስኬድ አልተቻለም ብለዋል።
👉 ዘላቂ መፍትሔ እና የደንብ ዝግጅት፦
የማንነት፣ የአሥተዳደር ወሰን እና ራስን በራስ የማስተዳደር ግጭት ማቆም ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የምላሽ አሰጣጥ ደንብ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል። በበጀት ዓመቱ በ6 አቤቱታዎች ላይ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ሰላም እንዲሰፍን መደረጉንም ጠቅሰዋል።
👉 የክልሎች ውይይት፦
በደቡብ ኢትዮጵያ እና በሲዳማ ክልሎች ሥር በሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች የተነሱ ጥያቄዎችን ክልሎቹ ራሳቸው ተወያይተውበት ወደ መጨረሻ መፍትሔ እንዲሄዱ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
👉 የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ ጉዳይ፦
ቋሚ ኮሚቴው በግልጽ ጥያቄ ሲቀርብባቸው በኖሩት በእነዚህ አካባቢዎች የተከናወኑ ሥራዎችን ለምን በሪፖርቱ አላካተተም? የሚል ጥያቄ ከምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል።
ለተነሳው ጥያቄ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጥላሁን ከበደ በሰጡት ምላሽ ዘንድሮ በተጨባጭ ሥራዎች ባይሠሩም ጉዳዩን በተመለከተ ግን በቂ ምላሽ መስጠት እንዲያስችል የተደራጀ መረጃን የመሰነድ ሥራ ተከናውኗል።
ይህም ቀጣዩ 7ኛው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱአለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleለተጎጂዎች ተስፋ የሰነቀው የባሕር ዳሩ የሴቶች እና ሕጻናት ማገገሚያ ማዕከል
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ነገ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ።