ለተጎጂዎች ተስፋ የሰነቀው የባሕር ዳሩ የሴቶች እና ሕጻናት ማገገሚያ ማዕከል

10
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በ123 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የሴቶች እና የሕጻናት ማገገሚያ እና ማቆያ ማዕከል አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አደርጓል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ሴቶች እና ሕጻናት እያጋጠማቸው ካለው የሥነ ልቦና ቀውስ፣ ጾታዊ ጥቃት እና ማኅበራዊ መገለል እንዲወጡ መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው ዋነኛ ተግባር ነው ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው ማዕከልም ተጎጂዎች ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ችግር እንዲያገግሙ፣ አስፈላጊውን የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ፣ የሕግ ከለላ እና ፍትሕ እንዲረጋገጥላቸው፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩላቸው በማድረግ ጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለመስጠት አቅም ይኾናል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ማዕከሉ በክልሉ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች እና ሕጻናት በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተገነባ ነው ብለዋል።
በክልሉ ለረጅም ጊዜ በቆየው ግጭት ሳቢያ ሴቶች እና ሕጻናት ለከፍተኛ የሥነ ልቦና እና ማኅበራዊ ቀውስ ተዳርገዋል ነው ያሉት።
በክልሉ በሚገኙ 20 ሆስፒታሎች ውስጥ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን እና አገልግሎቱም አጭር ጊዜን ብቻ ያማከለ እንደነበር አስታውሰዋል። በመኾኑም ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት የሚቆይ የሥነ ልቦና፣ የምግብ፣ የመኝታ እና የሕክምና ድጋፍ የሚሰጥበት ቋሚ ማዕከል ማቋቋም በማስፈለጉ ይህ ግንባታ ዕውን ሊኾን መቻሉን ነው የተናገሩት።
ማዕከሉን የተረከበው አጋር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ተጎጂዎችን ወደቀደመ ሕይወታቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንደሚወጣ ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ዶክተር አበራ አደባ ተናግረዋል።
ድርጅቱ በባሕር ዳር ከተማ በተገነባው አዲስ ማዕከል መግባቱ ይበልጥ ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ነው ብለዋል። ይህም ድርጅቱ በችግር የተጎዱ ወገኖችን ተረክቦ ጤንነታቸውን የመመለስ እና የማገገም፤ የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎችን የመስጠት፤ የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸት እና የራሳቸውን ቢዝነስ በመፍጠር ራሳቸውን የቻሉ አምራች ዜጎችን የማፍራት ኀላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችለው እንደኾነም ገልጸዋል።
ስምምነቱም በየሁለት ዓመቱ እየታደሰ የሚቀጥል ነው ብለዋል።
#የሴቶችናሕጻናትማዕከል#ባሕር_ዳር#አማራክልል#ባሕር_ዳር_ሰኔ_29_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአረንጓዴ አሻራ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ ኾኗል።
Next articleለምክር ቤቱ የሚቀርቡ የአሥተዳደር ወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ቁጥር መቀነሱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።