
በተፋሰስ ልማት አካባቢዎች የተተከሉ የተለያዩ ዕፅዋት ለንብ እርባታው መሳካት ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ የሚናገሩት አርሶ አደሩ ከተለመደው የሰብል ምርት ጎን ለጎን ንብ በማነብ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ምርት በመሠብሠብ ገቢያቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል። ዘንድሮም ተጨማሪ ችግኞችን በመትከል የሥራ መስካቸውን ይበልጥ ለማስፋት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ንጋቱ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በለሙ ተፋሰሶች በርካታ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች የንብ ሀብት ልማትን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ከ264 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር ስምለዓለም ምህረት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች የሚታዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ከ10 ነጥብ 61 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፤
የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ምርታማነትን ማሳደግ እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በተለይም በንብ ሀብት ልማት ብቻ በየዓመቱ ከ1ሺህ 200 በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ እየኾኑ ናቸው ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የአካባቢን ብዝኀ-ሕይወት ከመጠበቅ ባለፈ ለዜጎች ዘላቂ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑም ተመላክቷል።
#ባሕር_ዳር: ሰኔ 29/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
