
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ዐበይት ተግባራት እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከጎጃም ቀጣና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹሕ ሽፈራው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በማኅበረሰቡ ዘንድ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል። በተለይም የሴቶች ልማት ቡድን አደረጃጀቶችን በማጠናከር በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መደረጉን አንስተዋል።
በማኅበራት በማደራጀት የብድር እና ቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚ መደረጉንም ጠቁመዋል። ከዚህ ጎን ለጎን እናቶች በሥራ ገበታቸው ላይ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው በሁሉም ተቋማት የሕጻናት ማቆያዎችን በመገንባት ለሕጻናት የተሻለ አማራጭ የማቅረብ ሥራ ተከናውኗል።
የወጣቶች ዘርፍ ከሌላ ተቋም ወደ ቢሮው ከተዘዋወረ በኋላ ጠንካራ ተቋማዊ ውህደት በመፍጠር እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ተናባቢነት ያለው ዕቅድ እንዲወርድ ተደርጓል ነው ያሉት። የወጣቶች ስብዕና ግንባታ ማዕከላትም ከታለሙለት ዓላማ ውጭ እንዳይውሉ የማስተካከል ጅምር ሥራዎች ተካሂደዋል ብለዋል።
በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለጉዳት ለተዳረጉ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ችግር ውስጥ ለወደቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች የስነ-ልቦና ድጋፍ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች በስፋት ተሠርተዋል ነው ያሉት።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በመጠቀምም የበርካታ አረጋውያን ቤቶች መጠገናቸውን እና አዳዲስ መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።
የቀዳማይ ልጅነት፣ የኢትዮጵያ ኮደርስ እና የፋይዳ ፕሮግራሞች በርካታ ሴቶችን ተጠቃሚ ካደረጉ ዐበይት ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች መካከል በስኬት የተጠቀሱ ናቸው።
በቀጣይ ሴቶችን ከድህነት በማውጣት ራሳቸውን ችለው ለሀገር እና ለክልል የሚተርፍ አቅም እንዲገነቡ አደረጃጀቶቻቸውን ይበልጥ የማጠናከር ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም አንስተዋል።
ሀገራዊ እና ክልላዊ አስተሳሰብ ያለው፣ ስብዕናው በሚገባ የተገነባ ወጣት ትውልድ ለማፍራትም የወጣቶች ማዘውተሪያ ቦታዎችን ማመቻቸት እና ማዕከላትን የማጠናከር ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ባላቸው አቅም ልክ በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የኑሮ ሁኔታቸውን እንዲያሻሽሉ እና ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ በርብርብ ይሠራል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
