የኮረም፣ ዛታ እና ወፍላ ወረዳዎች «የእጉምርዳ ዘብ» ሰላም አስከባሪ ሚሊሻዎችን አስመረቁ።

6
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሥልጠና የወሰዱ የኮረም፣ ዛታ እና ወፍላ ወረዳዎች «የእጉምርዳ ዘብ» ሰላም አስከባሪ ሚሊሻዎች ተመርቀዋል።
ተመራቂዎቹ ባለፉት ስድስት ዓመታት የአካባቢያቸውን ሰላም ለማጽናት ሲታገሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
“ማንነት በግድ የሚወሰድ ዕቃ ወይም ግዛት አይደለም” ያሉት ተመራቂዎቹ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እና ሀገራዊ ስምምነቱን ለማክበር ሲባል ሰላምን መምረጣቸውን አብራርተዋል።
ዓለም አቀፍ የሰላም ስምምነትን የማያከብር ኀይል የዋግ ኽምራን እና የአማራ ክልል ሕዝብን አያከብርም ብለዋል።
በመኾኑም የኮረም፣ ዛታ እና ወፍላ ማኅበረሰብ የቀደመ ማንነቱን እንዲያገኝ መላው የአማራ ክልል ሕዝብ ሊደግፋቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ኀላፊ ኮሎኔል ዘመድኩን ወልደሥላሴ ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡት የሚሊሻ አባላት የአካባቢያቸውን ሰላም እና ጸጥታ በባለቤትነት በማስከበር፣ መንግሥት እና ሕዝብ የጣለባቸውን ኀላፊነት በብቃት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የዋግ ሕዝብ ትናንትም፣ ዛሬም ኾነ ነገ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን የቆመ ሕዝብ መኾኑንም ገልጸዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን “የእጉምርዳ ዘብ” ሰላም አስከባሪ ኀይሎች ጠላትን በመመከት እና የማንነት አንድነትን ለማስመለስ በሚያደርጉት ትግል ታላቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ለዚህም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።
Next articleከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እስከ ማኅበራዊ ደኅንነት