
የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በመደበኛ እና በተከታታይ ትምህርት በመምህርነት ሙያ ያሠለጠናቸውን 818 ተማሪዎች ለ14ኛ ጊዜ አስመርቋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል 332 የሚኾኑት ኮሌጁ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር ያሠለጠናቸው ናቸው። ቀሪዎቹ በዲፕሎማ መርሐ ግብር ሥልጠናቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ እና የኮሌጁ ሥራ አመራር ቦርድ ሠብሣቢ ቴዎድሮስ እንዳለው የመመረቅ ምሉዕነት የሚረጋገጠው ለማኅበረሰቡ በሚሰጠው ጥራት ባለው አገልግሎት መኾኑን ተናግረዋል።
ተመራቂዎች ትውልድን በዕውቀት የማነጽ፣ አመለካከቱን የማቃናት እና ገንቢ ትውልድ የመፍጠር ታሪካዊ ኀላፊነት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ሁሉም ፍላጎቶቻችን በሀገራችን ሕልውና ላይ የሚመሠረቱ ናቸው ያሉት አሥተዳዳሪው ተመራቂዎች ለሀገር ሰላም እና ልማት መትጋት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን ጌታቸው አድማስ ኮሌጁ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከ30 ሺህ በላይ ብቁ መምህራንን አሠልጥኖ በማስመረቅ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ሀገራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑን ተናግረዋል።
የዛሬ ተመራቂዎችም በኮሌጅ ቆይታቸው ከክፍል ውስጥ ትምህርት እስከ ተግባራዊ ልምምድ ለደረጃቸው የሚመጥን ዕውቀት እና ልምድ የገበዩ መኾናቸውን አንስተዋል።
ተመራቂዎች ይህንን ዕውቀት እና ልምድ በመጠቀም ትውልድን የመቅረጽ፣ ማኅበረሰቡን በቅንነት እና በታማኝነት የማገልገል ታሪካዊ አደራ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ በኮሌጅ ቆይታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዋንጫ እና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
#እንጅባራ: ሰኔ 29/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
