
#አዲስ_አበባ ሰኔ 29/2018 ዓ.ም
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የኹነቱን ሀገራዊ አንድምታ በሚመጥ መልኩ እየተከናወኑ መኾኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው የምክክር ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን፣ የተሳታፊዎችን መስተንግዶና ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
መግለጫውን የሰጡት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፤ አራት ሺህ ኢትዮጵያዊያን ከወረዳ፣ ከክልል፣ ከፌደራል ከተሞች እና ከውጭ ሀገራት ጉባኤውን ለመታደም ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ይጠበቃል ብለዋል።
ተሳታፊዎች የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የጸጥታ ጥበቃ እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለምክክሩ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።
የማደሪያ፣ የጸሎት ሥፍራና የምግብ ቦታዎች የተሳታፊዎችን ማኅበራዊ ደረጃ እንዲሁም ባሕል መሠረት በማድረግ መመቻቸታቸውንም አረጋግጠዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ለጉባኤው የሚሳተፉ ተወካዮች የሥራ ፍቃድ ለማግኘት እክል እንደገጠማቸው ለኮሚሽኑ ሪፖርት መቅረቡንም ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
ማንኛውም አካል ለምክክሩ ስኬት የሚጠየቀውን ኹሉ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ያስገነዘቡት ፕሮፌሰር መሥፍን፤ ኹሉም ሰው ለምክክሩ ተሳታፊዎች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር በኮሚሽኑ ስም አሳስበዋል።
ሀገራዊ ጉባኤው ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚሳተፍበት በመኾኑ፤ በሀገራችን ታሪክ ልዩ ምዕራፍ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ተመካካሪዎች ይህን ታሳቢ በማድረግ በምክክር ጉባኤው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ከሐምሌ 1 ጀምረው አዲስ አበባ በመግባት እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ ኹሉም ኢትዮጵያዊ በባለቤትነት የሚሳተፉበት መኾኑን ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙኃን ለሂደቱ ስኬት የላቀ ድርሻቸውን የመወጣት ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ኮሚሽነር መላኩ፤ ምክክሩ አንድ አካል ብቻ የሚወስንበት ሳይኾን ኹላችንም ድርሻችንን የምንወጣበት ነው በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተመካካሪዎች በተቀረጹት አጀንዳዎች ላይ ተወያይተው ከሚደርሱበት ድምዳሜ በፊት ምንም ዓይነት ውሳኔ አይኖርም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ከታየው በላቀ ደረጃ ተመካካሪዎች በነፃነትና በጥልቀት እንደሚወያዩም ጠቁመዋል።
በምክክር የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ልክ እንደሚንቀሳቀስም ገልጸዋል።
በመግለጫው ላይ የተገኙ ጋዜጠኞችም ጥያቄዎችን ጠይቀው በኮሚሽነሮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
