የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ይገባል።

5

 

በአማራ ክልል በግብርና፣ በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ “ዘመናዊ ግብርና ለሁለንተናዊ ልዕልና” በሚል መሪ መልዕክት በምሥራቅ አማራ ቀጣና ለሚገኙ የዞን እና የወረዳ ግብርና እና የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መሪዎች፣ ከቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ግብርናን በዘማናዊ የምርት አመራረት ተግባራዊ በማድረግ ትራንስፎርሜሽኑን ማረጋገጥ እንዲቻል መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ እና እንዲዘምን በሚሠሩ ሥራዎች ላይ መግባባት ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማትን እና ዘመናዊ ግብርናን መሠረት በማድረግ ወደ ሁለንተናዊ ልዕልና ለመሸጋገር የሚያስችሉ፣ የግብርናን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያግዙ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም መድረኩ ወሳኝነት እንዳለው ተጥቅሷል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ መድረኩ በግብርና መዋቅር ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ወጥ የኾነ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።

በመድረኩ በ25 ዓመቱ የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ ላይ በመመስረት የወደፊት ትልሞችን በጋራ መገምገም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በተለይም ከ2018 ዓ.ም. ጀምሮ የተከናወኑ ጠንካራ ጎኖችን ለሌሎች ልምድ እንዲኾኑ ማጋራት እና ጉድለቶችን ለይቶ ማረም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ የተጀመሩ የኢኒሼቲቭ ሥራዎችን ማጠናከርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን እሴት በሚጨምር መልኩ ለመተግበር የሚያስችል መድረክም መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ግብርናን አስተማማኝ ለማድረግ ወንዞችን እና የከርሰ ምድር ውኃ ጸጋዎችን በመጠቀም የፍራፍሬ፣ የአትክልት ልማትን ማዘመን እና የመስኖ ልማት ዕቅድ ውጤታማ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ነው የጠቆሙት፡፡

ባለሙያዎች የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር በቁርጠኝነት፣ በቅንነት እና በከፍተኛ የኀላፊነት ስሜት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሚኮ_ዜና #ግብርና #አማራ_ክልል
#ደሴ: ሰኔ 29/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ፦ደጀን አምባቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleመንግሥት ግትር እና ተላላኪ ጽንፈኛ ቡድን ላይ ቀጣይነት ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ይወስዳል።
Next articleየአፍሪካ የሕክምና ትምህርት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።