መንግሥት ግትር እና ተላላኪ ጽንፈኛ ቡድን ላይ ቀጣይነት ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ይወስዳል።

11

 

የአማራ ክልል መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ሰላም ለሀገራችንም ኾነ ለክልላችን ሁለንተናዊ ልማትና ሕልውና መሠረት ነው ብሏል።

ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ እንደ እስትንፋስ እጅግ አስፈላጊ ተፈጥሯዊ ጸጋ ነው። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ወልዶ መሳም፣ ዘርቶ መቃም፣ ሰርቶ መክበርና ማደግ ከቶውንም አይታሰብም ነው ያለው።

በክልላችን ባለፉት ሥስት ዓመታት በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት በሕዝባችን ላይ ከፍተኛና ዘርፈ-ብዙ ሁለንተናዊ ጫና ደርሷል። በዚህም ሳቢያ የውድ ዜጎቻችን ሕይወት በከንቱ ጠፍቷል፤ የሕዝብ መጠቀሚያ የኾኑ ታላላቅ መሠረተ-ልማቶች ወድመዋል፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሕፃናት ልጆቻችን ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው እንዲቀሩ ኾኗል፤ ትርፍ አምራች የኾነው አርሶ አደራችን ምርቱን በነፃነት ወደ ገበያ እንዳያቀርብ እንቅፋት ኾኖታል፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት በማስተጓጎል፣ ለአርሶ አደሩ የሚቀርበውን ሰው ሰራሽ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ ማድረስ እጅግ ፈታኝ ኾኖ አልፏል።

የዚህ ሁሉ ውድመት፣ ግጭት እና የሕዝብ ሰቆቃ መሪ ተዋናይና ጠንሳሽ የኾነው ጽንፈኛው ተላላኪ ቡድን ነው። ይህ ቡድን ይሄንን ሁሉ ግፍና በደል በሕዝባችን ላይ የፈፀመው “ሥልጣን በሕጋዊ ምርጫ ከሕዝብ የሚመነጭ መኾኑ እየታወቀ በአፈሙዝ የመንግሥትን ኃላፊነት እይዛለሁ” በሚል ቅዠት ነው። ከ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሠለጠነ አስተሳሰብ ጋር ፍፁም በተጋጨ የኋላቀርነት አባዜ ተገፋፍቶ መኾኑ ግልፅ ነው።

የክልላችንን ሕዝብ ከዚህ እኩይና ጽንፈኛ ቡድን ሰለባነት ለመታደግና የተሟላ ሰላም ለማስፈን በተወሰደው የተቀናጀ የሕግ ማስከበር እርምጃ፤ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልላችን የፀጥታ አካላት በጥምረት ውድ ሕይወታቸውን በመገበር ባከናወኑት ስኬታማ ሕግ የማስከበር ሥራ በሕዝባችን ላይ ተደቅኖ የነበረው ከፍተኛ አደጋ ተቀልብሷል። በዚህም አሁን የሚታየው አንፃራዊ ሰላም ሊሰፍን ችሏል።

መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት እና የሕግ የበላይነትን የሚረጋገጠው በኀይል አማራጭ ብቻ ነው ብሎ አያምንም። በመኾኑም በተሳሳተ መንገድ ተደናግረው ጫካ ለገቡ ኃይሎች በሙሉ እይታና በቅን ልቦና በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አቅርቧል። በዚህም ምክንያት የሰላም ጥሪውን መነሻ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጥቀው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ጥሪውን በመቀበል ወደ መንግሥት በመግባት ማኅበረሰባቸውን ተቀላቅለዋል። ታጣቂዎቹ ወደ ሰላም አማራጭ ለመመለስ በወሰዱት ጠንካራ ውሳኔም የሕዝባቸውን ሰላም ማረጋገጥ ብቻ ሳይኾን ራሳቸውንም ከተሳሳተ አጥፊ መንገድና ከተላላኪነት ነፃ አውጥተዋል፡፡

በአንፃሩ፤ የመንግሥትን የሰላም ጥሪና ትዕግስት እንደ ፍርሃት በመቁጠር፤ አሁንም ድረስ በሕዝባችን ላይ ዝርፊያ፣ እገታ እና አላስፈላጊ ትርምስ ለመፍጠር ሌትና ቀን የሚሠሩ ኃይሎች አሉ። እነዚህ ፅንፈኛ ቡድኖች ከሕዝባችን ታሪካዊ ጠላቶች በተለይም ከአጥፊው ቡድን ህወሐት ጋር በመተባበር የአማራን መሠረታዊ ጥያቄና በደምና በአጥንት ያስመለሳቸውን እና ቀሪ ሕጋዊ ጉዳዮችን ለማስጨረስ ከሃገሪቱ ሕዝቦች ጋር በመመካከር ላይ የምንገኘውን የወሰንና ማንነት ጉዳዮች አሳልፎ በመስጠት ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ በሚል ሽፋን እኩይ ድርጊቱን በመቀጠል ላይ ይገኛል።

መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ እና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ቀዳሚና ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በእነዚህ ግትርና ተላላኪ ፅንፈኛ ቡድን ላይ ቀጣይነት ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ይወስዳል፤ እየተወሰደም ይገኛል። ከሕግ ማስከበር ሥራችን ጎን ለጎንም የሰላም አማራጭን ለሚቀበሉ ታጣቂዎችም መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ጥሪ እና በሩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡

የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ በሚደረገው መጠነ-ሰፊ ርብርብ እና አሁን የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ አስተማማኝ ሰላም እንዲሸጋገር መላው የክልላችን ሕዝብ የተለመደውን ድጋፍና ንቁ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ
ባሕር ዳር

#ሰላቂሰላም #የሕግ_ማስከበር#

#ባሕር_ዳር_ሰኔ 29_2018ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleጤናማ አፍሪካን የመገንባት ጉዞ 🩺🌍
Next articleየምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ይገባል።