
ለበርካታ አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጥቂት የልሂቃን ስብስቦች ፍላጎት እና ትረካ የተጠለፈ ነበር። በዚህም እንደ ፍትሕ እና እኩልነት፤ ልማት እና መልካም አሥተዳደር ያሉ እውነተኛ እና መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን ወደ ጎን በመተው በሕዝብ ስም የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ በመቅረጽ እና ጥያቄዎችን ወደ ብሔር እና ሃይማኖት ተኮር ልዩነቶች በማዞር ሀገሪቱን የግጭት እና የቅሬታ አዙሪት ውስጥ አስገብተዋት ቆይተዋል።
አንዳንዶች ደግሞ ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ ከማፍለቅ ይልቅ የሀገሪቱን የፖለቲካ ውስብስብነት እና የሚያስከትለውን መዘዝ በመፍራት ራሳቸውን ከፖለቲካው አግልለው ቆይተዋል።
እነዚህን ሁሉ ችግሮች ያለመፍትሔ አርግዛ እና አዝላ መጓዝ ኢትዮጵያን ጤና ነስቷት ቆይቷል። አሁን መፍትሔ ተዘይዷል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየሠራ ነውና።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አለመግባባቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ተፈትተው ዘላቂ ሰላም፣ ብሔራዊ አንድነት እና መግባባት ተፈጥሮ መገላገል ይገባታል በሚል ዓላማ አንግቦ እየሠራ ነው።
በመላው ሀገሪቱ ከ200 ሺህ በላይ ከሚኾኑ ኢትዮጵያውያን ጋር በመወያየት፣ አጀንዳዎችን አሰባስቧል። ዋና ዋና አጀንዳዎችን የመለየት እና በአጀንዳዎቹ ላይ ተመካክሮ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሐምሌ ስምንት ቀን ቀጠሮ ይዟል። ኢትዮጵያ ያዘለችውን ችግር ለማራገፍ፤ ያረገዘችውን መፍትሔ ለማገላገል እየሠራ ነው።
በተለይ አጀንዳዎችን ከባለቤቱ በመሰብሰብ እና የልሂቃኑን የሕዝብ አጀንዳ የመጠምዘዝ የቆየ ልምድን ከማስቀረት አኳያ ስኬታማ ሥራ እየሠራ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በቅርቡ ስምንቱን ዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ይፋ ባደረጉበት ዕለት አጀንዳዎቹ ከላይ ወደ ታች የተጫኑ ሳይኾኑ ከራሱ ከሕዝቡ ድምጽ፤ ፍላጎት እና ስጋት የተቀዱ ናቸው ብለዋል።
አጀንዳዎቹ ከራሱ ከሕዝቡ የተቀዱ፤ መፍትሔዎቹም ከሕዝብ የሚመነጩ መኾናቸውም ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን የሕዝብን አጀንዳዎች ለራሳቸው የሥልጣን እና የቡድን ፍላጎት ማሳኪያ አድርገው የመጠቀም የቆየ ልምድን ያስቀረ እና በሀገር ዕጣ ፈንታ የባለቤቱ የሕዝቡ ድምፅ ሳይካተት የመቅረቱን የታሪክ ክፍተት የዘጋ ታሪካዊ ምዕራፍ ኾኗል።
የሕዝቡ ተሳትፎ በምክክሩ ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮችን በመዘርዘር ብቻ የሚቆም አይደለም። ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላም እና ዕርቅ የምትሻገርበትን የመፍትሔ አቅጣጫዎችም በራሱ አንደበት እንዲያስቀምጥ ተደርጓል። በቀጣይም በተመረጡ ተወካዮቹ አማካኝነት በዋናው የምክክር ጉባኤ ተሳታፊ ኾኖ የመፍትሔው አካል ይኾናል ነው ያሉት።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም በሂደቱ ተሳታፊ ናቸው። ሀገር በቀል ዕውቀቶችም በሕዝብ የቀረቡ አጀንዳዎችን ለመፍታት እንደአስፈላጊነታቸው አገልግሎት ላይ ይውላሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) እንደሚሉት ምሁራን በተለያየ መስክ ያካበቷቸውን ዕውቀቶች ተጠቅመው ለተሳታፊ ዜጎች በተለያዩ ጽንሰ-ሀሳቦች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የምክክር ኮሚሽኑን ያግዛሉ ብለዋል። ፖለቲካን በሩቁ ከማለት ወጥተው ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓት መሻሻል የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
በዚህ መልኩ ለዘመናት በነፍጥ እሳቤ የደማችው ሀገር እና የቆሰለው ሕዝብ በራሱ ውሳኔ ተመካክሮ እና ተደማምጦ ዘላቂ ፈውስ ያገኛል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ሆይ ችግርሽ ከጀርባሽ ይራገፍ፤ ያረገዝሽው የአንድነት፣ የሰላም እና የልማት ተስፋ በሰላም ይገላገል! 🙏🕊️
#AMECO #ኢትዮጵያ #ሀገራዊምክክር #Ethiopia #NationalDialogue
#ባሕር_ዳር#ሰኔ29_2018ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
