
የተመካከሩ ሀገር አጽንተዋል፤ የተመካከሩ ሰላምን ጠብቀዋል፤ የተመካከሩ ጦርነትን አርቀዋል፤ ግጭትን አስቀርተዋል፤ በአንድነት የቆሙ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ነስተዋል፤ በታሪክ ፊት የከበረ እና የታፈረ ታሪክ ሠርተዋል፤ ነጻነታቸውን አስከብረዋል፤ ሉዓላዊነታቸውን አጠናክረዋል፡፡
የተመካከሩ ልብ ለልብ ተገናኝተዋል፤ የችግሮቻቸውን ጥልቀት፤ የተስፋቸውን ምጥቀት ለይተዋል፤ ሕመማቸውን እና ተስፋቸውን ተረዳድተዋል፤ ለጋራ ሀገራቸው የጋራ መፍትሔ አስቀምጠዋል፤ ነጋቸውን በጋራ አሳምረዋል፤ ሀገራቸውን ከችግር እና ከፈተና አሻግረዋል፤ በአንድነት የቆሙ ዓለምን ያስደነቀ ገድል ፈጽመዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ጸንተው፤ እስከ ሞት ድረስ ታምነው፤ ከሁሉም በፊት ሀገራቸውን አስቀድመው ሲያኮሯት ኖረዋል፡፡ በዓለም ታሪክ የከበረውን ሠርተዋል፤ በአንድነት ዓድዋን የመሰለ ገድል ፈጽመዋል፤ ልብ ለልብ በመገናኘት፣ ለአንድ ሀገር በኅብረት በመጽናት የቅኝ ግዛትን ወረራ በጀግንነት መክተዋል፤ በአሸናፊነት ተወጥተዋል፤ ለጥቁር ዘር ሁሉ አብነት ኾነዋል፤ የቅኝ ገዢዎችን ጉዞ ገትተዋል፤ የቅኝ ገዢዎችን ሕልም አምክነዋል፡፡
ልብ ለልብ ባይገናኙ፣ ከሁሉም በላይ ሀገርን እና ሠንደቅ ዓላማን ባያስቀድሙ፣ በአንድነት ባይነሱ ኖሮ ዓድዋ አይገኝም፤ ጠላትም ድል አይኾንም፤ ነጻነትም አይኖርም ነበር።
ኢትዮጵያውያን ችግር በገጠማቸው ጊዜ ዛፍ ሥር ተቀምጠው እየተመካከሩ፤ የጋራ መፍትሔ እየዘየዱ፤ በዳይ እንዲክስ፤ ተበዳይ እንዲካስ እያደረጉ፤ ጥል እና ጥላቻን እያራቁ ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ከዛፍ ሥር ተቀምጠው ግጭትን አድርቀዋል፡፡ ከዛፍ ሥር ተቀምጠው ነውርን አውግዘዋል፡፡ ከዛፍ ሥር ተቀምጠው ለግድያ የተፈላለጉ ነፍሳትን አስተቃቅፈዋል፡፡ ከዛፍ ሥር ተቀምጠው የሰላምን ተክል ተክለዋል፡፡ የፍቅርን ምንጭ አፍልቀዋል፡፡
”አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው እንደተባለ አባቶች እና እናቶች ለልጅ የሚበጀውን ሥርዓት እያበጁ፤ ለሀገር የተገባውን ሥርዓት እያሰረጹ ኢትዮጵያ በጽናት፣ በአንድነት እና በነጻነት እንድትኖር አድርገዋል፡፡ ዛፍ ሥር እየተቀመጡ እየተመካከሩ የማያልፉ የሚመስሉ ጊዜያትን አሳልፈዋል፤ ግጭትን እና ጦርነትን ወደ ፍቅር እየለወጡ ሀገር እና ሕዝብ ጠብቀዋል፡፡
ከዛፍ ሥር እየተሰባሰቡ ሰላምን ሲሰብኩ፣ ጥልን ሲያርቁ የኖሩት ኢትዮጵያውያን አሁን ደግሞ በችግሮቻቸው ላይ በጋራ ለመምከር ሀገራዊ ምክክር አዘጋጅተዋል፡፡ ምክክሩ የትናንት እርሾ ያለው፤ የኢትዮጵያን ባሕል እና እሴት፣ ታሪክ እና ሃይማኖት የጠበቀ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ የፖለቲካ ስብራቶችን፣ የትርክት መዛነፎችን፣ ለሀገር እና ለሕዝብ አሜካላ የኾኑ ሰንኮፎችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር አቋቁመው ሢሠሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ይህ ቀጠሮ ኢትዮጵያ እልፍ ጉዳዮችን የምታተርፍበት፤ የምክክር ባሕልን የምትተክልበት፤ የግጭትን አባዜ የምትነቅልበት፤ የጦርነት እሳቤ የምታደርቅበት፤ የአንድነት ገመድን የምታጠነክርበት፤ ኢትዮጵያዊነትን የምታስጌጥበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድኅን ሀገራዊ ምክክር የሁላችንም ነው፤ ሁላችንም ባለቤቶች ነን ይላሉ፡፡ ኮሚሽኑ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ አካታችነትን የማረጋገጥ ሥራ ሠርቷል፤ የሀገራዊ ምክክር አንደኛው መርሕ አካታችነት ነው ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ በሁለት መልኩ አካታችነትን አረጋግጧል፤ አንደኛው የሃሳብ አካታችነት፤ ሁለተኛው ደግሞ ውክልና አካታችነት ነው፡፡
ምክክሩ ሃሳብን እ ውክልናን እያካተተ እና እያረጋገጠ የሄደ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዬ ነው የሚሉትን ሁሉ እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥቷል፤ ሃሳባቸውንም ተቀብሏል። ሃሳባቸው ብቻ ሳይኾን ውክልናም እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን ሠርቷል ነው የሚሉት፡፡
ኢትዮጵያውያን ምን ላይ እንምከር ? በምን ጉዳይ ተመካክረን እንግባባ? ብለው ተወያይተው አጀንዳቸውን አሰባስበዋል ይላሉ፡፡ በአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቱ መደማመጥ የነበረበት እና አንደኛው የሌላኛውን ሃሳብ የተረዳበት ነበር ብለዋል። ምክክሩ ኢትዮጵያውን በባለቤትነት የያዙት እንደሆነም ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጋራ ውጤታማ የሚያደርገን፣ የጋራችን ነው፤ አንደኛው አዘጋጅ አንደኛው ተሳታፊ አይደለም፤ የጋራ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክር ሂደቱ ግልጽ፣ ገለልተኛ፣ አሳታፊ እና አካታች በኾነ መልኩ እንደተመራ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምንሻውን ያክል ወደፊት እንዳትራመድ ቋጠሮዎች ሊፈቱ የሚችሉት በምክክር ብቻ መኾኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠው ትኩረት እና ተሳትፎ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያውያን ታሪክ የማይዘነጋው ሀገራዊ ኀላፊነት ተውጥተዋል፣ እየተወጡም ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ ቀጣዩ ጉዧችን በዋና ዋና ሀገራዊ አጅንዳዎች ላይ በሠለጠነ መንገድ መመካከር እና ዘላቂ መግባባት ላይ መድረስ ነው ብለዋል።
በውጤቱም እርስ በእርስ ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል፣ መተማመን እንዲፈጠር፣ መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮቻችን ተፈትተው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሠረት እንጥላለን ብለዋል፡፡
#ሀገራዊምክክር #የኢትዮጵያምክክር #ሀገራዊመግባባት #አንድነት #ሰላምናመግባባት #NationalDialogue #EthiopianDialogue #UnityInDiversity
#ባሕር_ዳር_ሰኔ_28/2018ዓ_ም
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
