
የከሚሴ መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ እና በዲግሪ መርሐ ግብር ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ ጀማል አሊ በሀገር ግንባታ ውስጥ የትምህርት ተቋማት ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጎችን የማፍራት ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል። በዚህ ዓመት የከሚሴ መምህራን ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ መርሐ ግብር ማስመረቁ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ተመራቂዎች ወደ ሥራ ሲገቡ የወጡበትን ማኅበረሰብ በተገቢው እንዲያገለግሉም አሳስበዋል። ዕውቀታችሁን ለሀገር ግንባታ አውሉ ነው ያሉት።
የከሚሴ መምህራን ኮሌጅ ዲን ጀማል እንድሪስ (ዶ.ር) ኮሌጁ ላለፉት ዓመታት ከ13 ሺህ በላይ መምህራንን በማስመረቅ ወደ ሥራ ማስገባቱን ገልጸዋል። ዛሬ በዲፕሎማ 266 ተማሪዎችን እና በዲግሪ መርሐ ግብር 79 ተማሪዎችን ማስመረቁን አስረድተዋል።
ኮሌጁ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጥናቶችን በማዘጋጀት እና ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ሢሠራ መቆየቱን ነው የገለጹት።
የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት ማኅበረሰባቸውን በትጋት እንዲያገለግሉ አስገንዝበዋል።
በኮሌጁ በማዕረግ የተመረቁ ምሩቃን በቆይታቸው በቂ ዕውቀት መቅሰማቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ወደ ሥራ ሲገቡ በከፍተኛ መነሳሳት ማኅበረሰባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
የከሚሴ_መምህራን_ኮሌጅ #የመጀመሪያ_ዲግሪ #እጩ_መምህራን #KemissieTeachersCollege #FirstDegreeGraduation #FutureTeachers #Kemissie #ከሚሴ#ሰኔ27/2018ዓም
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
