
🌍 ዛሬ የምንተነፍሰው እያንዳንዱ አየር፤ የምንጠጣው እያንዳንዱ ጠብታ ውኃ እና የምንረግጠው መሬት ሁሉ የሕይወታችን ዋስትናዎች ናቸው።
ተፈጥሮን መንከባከብ ማለት የራሳችን እና የልጆቻችንን ሕልውና ማቆየት ማለት ነው። ዛሬ በተፈጥሮ ላይ የምናደርጋት አንዲት ትንሽ በጎ ተግባር ለነገው ትውልድ ትልቅ ተስፋን ትሰንቃለች።
“መሬት አይከዳም” እንዲሉ አበው መሬት የሰጧትን በበረከት የምትመልስ፤ የዘሩባትን አብቅላ የምትመግብ ታማኝ እናት ናት።
👉 ታዲያ ይህችን ታማኝ እናት ዛሬ ምን ያህል እየተንከባከብናት ነው?
ተፈጥሮን መጠበቅ ማለት ለአፈር፣ ለዛፉ እና ለወንዙ ብቻ የምናደርገው በጎነት አይደለም፤ ለራሳችን የምንሰጠው ክብር እና የምናሳየው የንቃት ደረጃ መገለጫ እንጂ።
በአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ እና ማኅበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ ዳይሬክተር አብርሃም ማርዬ የተፈጥሮ ሥነ-ምኅዳር ሚዛንን መጠበቅ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ሕልውና፤ ለአካላዊ ጤንነት እና ለቅን አዕምሯዊ አስተሳሰብ ግንባታ ቀጥተኛ እና ወሳኝ ሚና ያለው ነው ይላሉ።
በተፈጥሮም ኾነ በመንፈሳዊው እሳቤ እፅዋት እና እንስሳት ከሰው ልጅ መፈጠር አስቀድመው የተገኙ ናቸው። የሰው ልጅ የእነዚህ ጸጋዎች ተጠቃሚ ብቻ ሳይኾን ተንከባካቢ እና ጠባቂ የመኾን ታሪካዊ ኀላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል።
🌿 ነገር ግን ይላሉ ዳይሬክተሩ የሰው ልጅ ያለ እፅዋት ኦክስጅን ለሰከንዶች እንኳ መኖር የማይችል ቢኾንም ለእፅዋት የሚሰጠው ትኩረት ግን አሁንም አነስተኛ ነው። ማኅበረሰቡ እፅዋትን ለኢንዱስትሪ እና ለምግብ ግብዓትነት ብቻ የመመልከት አዝማሚያ ቢኖረው እንኳ ጥቅማቸው ግን ከዚያ የላቀ ነው ብለዋል።
የሰው ልጅ ቅንነት እና የተረጋጋ ባህሪ የሚገነባው ተፈጥሮ በተሟላበት አካባቢ ሲኖሩ ብቻ ነው ይላሉ። ተፈጥሮ ሲደፈርስ የሰው ልጅ ባህሪም አብሮ ይለወጣል ብለዋል።
አሁን ላይ የሰው ልጅ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ በተፈጥሯዊ ሚዛን ላይ ትልቅ ጫና እየተፈጠረ ይገኛል ነው ያሉት። ቀደም ሲል የሰው ልጅ ስለ ራሱ የዕለት ከዕለት ሥራ ብቻ ይጨነቅ የነበረ ቢኾንም አሁን ላይ ግን ትልቁ ጭንቀት የተሰጡንን የተፈጥሮ ጸጋዎች በአግባቡ ስላለመያዛችን ሊኾን ይገባል ብለዋል።
💨 🌿 ወደፊት በዓለም ላይ የአረንጓዴ እፅዋት፣ የውኃ፣ የንጹሕ አየር እና ስፔስ በሥነ-ምሕዳር ውስጥ ዋነኛ መወሰኛ እየኾኑ ይመጣሉ ነው ያሉት።
💚 አረንጓዴ አሻራ ዝም ብሎ ለዐይን ደስ የሚል ልምላሜ ለመፍጠር ብቻ ሳይኾን የሰውን ልጅ አጠቃላይ አስተሳሰብ እና ሕልውና ለመጠበቅ ሲባል በጥልቀት ሊታሰብበት የሚገባ ታላቅ ተግባር እንደኾነም ነው የገለጹት።
#አረንጓዴአሻራ #ተፈጥሮ #ሕልውና #አረንጓዴሕይወት #GreenLegacy #Nature #Ecology #Ethiopia
#ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
