የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

2

 

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥራዎች በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ነው የተፈራረሙት።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመማር መስተማር፣ በጥናት እና ምርምር፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ አጋርነት የሚያከናውናቸው ሥራዎች እንደ ሀገርም የሚታወቁ እና ሥመጥር ዩኒቨርሲቲ መኾኑን ገልጸዋል። ከእንደዚህ ዓይነት ተቋም ጋር መሥራት አጠቃላይ የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።

ማኅበራዊ አገልግሎትን ለመወጣት ዩኒቨርሲቲዎች መሳተፍ አለባቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዚህ ረገድ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የክልሉን አጠቃለይ የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል እና የፍትሕ ዘርፉ እንዲጠናከር ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን አንስተዋል።በዋናነት የዳኝነት ሥራዎችን ተደራሽ ለማድረግ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን የማጠናከር፤ የሕግ አገልግሎትን የማስፋት ሥራ በሰፊው እየተሠራ ነው ብለዋል።

ይህን ማጠናከር የአካባቢውን የሽምግልና እና የእርቅ ባሕል ጠብቆ ከማቆየት አኳያ ፋይዳው የጎላ በመኾኑ ሀገር በቀል ዕውቀቱን የማጠናከር እና የማስፋፋት ሥራ ከዩኒቨርሲቲው ጋር እንሠራለን ብለዋል።

በሕግ አገልግሎት የጠበቆችን አቅም በመገንባት፤ ተቋም ግንባታ ላይ የባለሙያ እና የመሪዎችን አቅም በመገንባት፣ የሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት፣ በዲጅታላይዜሽን ዜጎች ባሉበት አካባቢ ኾነው የፍትሕ አገልግሎት እንዲያገኙ የተጀመረውን ጠንካራ ሥራ እስከታች ለማስፋት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ሠፋፊ ሥራዎችን በትብብር እንሠራለን ነው ያሉት።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሥራት አፀደወይን (ዶ.ር)
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል ይታወቅ የነበረው በጤናው ዘርፍ ነበር ብለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከ350 በላይ መርሐግብሮችን እየሰጠ መኾኑን እና ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሕግ ትምህርት ቤት መኾኑን ነው የገለጹት።

ዩኒቨርሲቲው 18 የሚኾኑ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማዕከላት እንዳሉት ገልጸዋል። የሕግ ትምህርት ቤቱ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በሌላ ቦታ የማይገኙ የሕግ መርሐግብሮች እንዳሉት ተናግረዋል። ከፍትሕ ሥርዓቱ ጋር ተያያዥ የኾኑ የአቅም ግንባታ፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እና ቴክኖሎጅዎችን የማበልጸግ ሥራም እየሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ጋር ይሠራል ነው ያሉት። የክልሉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት በጋራ ብንሠራ የበለጠ ውጤት እናገኛለን በሚል በጀመራቸው አሠራሮች ውጤት አምጥቷል ብለዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን ያከናወናቸውን አጠቃላይ የለውጥ ሥራዎች ያደነቁት ፕሬዝዳንቱ ሥምምነቱ በሰው ኀይል ልማት እና በተማሪዎች የተግባር ልምምድ በጋራ በመሥራት ጥራት ያለው ትውልድ ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደምም በአቅራቢያ ከሚገኙ ፍሬድ ቤቶች ጋር እንደሚሠሩ አንስተዋል። ይህን የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ ዕቅድ ወጥቶላቸው ከሠራን ተቋማትን ብቻ ሳይኾን ክልሉን እና ሀገሪቱን የሚያሳድጉ ተምሳሌታዊ ሥራዎችን መሥራት እንችላለን ብለዋል።

በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መሪዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያከናወናቸውን የለውጥ ሥራዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

#አሚኮ_ዜና #በጋራ_መሥራት #ጠቅላይ_ፍርድ_ቤትና_ጎንደር_ዩኒቨርሲቲ #አማራ_ክልል
#ባሕር_ዳር፡ ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበሐረሪ ክልል በሙሉ ድምፅ የጸደቀው እና ወደ ምክር ቤት የተመራው ረቂቅ በጀት! ✨🏛️
Next article” መንግሥት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂካዊ ፖሊሲዎችን እና ፕሮግራሞችን በቁርጠኝነት እየተገበረ ነው” ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር