
የሀረሪ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት የ2019 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት ረቂቅ በጀት ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲኾን ውሳኔ አሳተላልፏል፡፡
ካቢኔው በክልሉ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የቀረበለትን የ2019 የበጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ በጥልቀት በመወያነት እና ግብዓት በማከል ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል።
በዚህም መሰረት በክልል ደረጃ ከተያዘው በጀት 60 በመቶ ለካፒታል በጀት የተመደበ ሲኾን 38 በመቶው ደግሞ ለመደበኛ በጀት የሚውል ነው ተብሏል።
የበጀቱ ምንጭም በዋናነት በክልሉ ከተለያዩ ገቢዎች የሚሰበሰብ ገቢ እና ከፌዴራል መንግሥት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማ እና ከሌሎች ምንጮች ታሳቢ መደረጉም ተነስቷል።
በጀቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም የ33 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ነው የተገለጸው።
የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ በ2018 በጀት ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ እና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
በተለይም በገጠር እና በከተማ የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ሊመልሱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ነው ያመላከቱት።
ለገጠር እና ለከተማ ኮሪደር ልማት፣ ለንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ ለትምህርት እና ለጤና ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ነው ያሉት።
በጀቱ ቁጠባን መሰረት በማድረግ በተለይም የሕዝቡን ሕይወት በሚያሻሽሉ እና መሠረታዊ ጥያቄን በሚመልሱ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
በድህነት ቅነሳ ዘርፎች ላይ ርብርብ እንደሚደረግም አመላክተዋል።
በወረዳ ደረጃ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ለማስጀመር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ያመላከቱት ርእሰ መሥተዳድሩ በዚህም ለኅብረተሰቡ ፈጣን፣ ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
በክልሉ ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አንጻር በትኩረት መንቀሳቀስ ወሳኝ መኾኑን ጠቁመው ለዚህም የክልሉ ኢኮኖሚ በሚያመነጨው ልክ በታቀደው ልክ መሰብሰብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱም በቀረበው የ2019 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ነው ወደ ክልሉ ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ የወሰነው።
#HarariRegion #DraftBudget2019 #RegionalCapital
#ባሕር_ዳር: ሰኔ 27/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
