“የሰው ልጅን በዕኩል ዐይን የሚያገለግል ሆስፒታል ይገነባል” ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ

7

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ አንድነት ገዳም የአራቱ ጉባያት የመጻሕፍት ምስክር ትምህርት ቤት በባሕር ዳር ከተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል።

ቤተ ጉባኤው ሐዋሪያዊ ትምህርት ከመስጠት እና ደቀመዛሙርትን ከማፍራት በተጨማሪ በባሕር ዳር ከተማ ደረጀውን የጠበቀ ጠቅላላ ሆስፒታል ለመገንባት ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር 30 ሺህ ካሬ ቦታ ተቀብሎ ሥራውን ለመጀመር የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል።

በማስጀመሪያ በመርሐ ግብሩ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብጹዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብጹዕ አቡነ ዘካሪያስ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብጹዕ አቡነ ኤልያስ የስካንዲቪያን እና የኖርዲክ ሀገራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአራቱ ጉባያት መምህር ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ የሰው ልጅን በእኩል ዐይን የሚያገለግል፣ ጥልቅ የሕክምና ዕውቀትን በመያዝ ታካሚዎችን የሚፈውስ፣ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋ የሚሰጥ እና በሱስ የተጎዱ ወገኖችን ከሱስ ለማላቀቅ የሚያስችል ሆስፒታል እንደሚገነባ ተናግረዋል። ሆስፒታሉ ሆስፒታል ብቻ ሳይኾን የሕክምና መንደር እንደኾነም አብራርተዋል።

ሆስፒታሉ በውስጡ የአዕምሮ ሕክምና፣ የእናቶችና ሕጻናት፣ የልብ፣ የኩላሊት፣ የካንሰር ጠቅላላ ሕክምና እና ሌሎች ማዕከሎችን የያዘ ነው ብለዋል።

በሆስፒታሉ ሀገር በቀል የመድኃኒት ቅመማን ከዘመናዊ ጋር ለማቀናጀት ምርምር የሚካሄድበት ማዕከልም እንደሚኖር ገልጸዋል። ማኅበረሰብን ያለምንም ልዩነት በእኩል የሚያገለግል የሕክምና ትምህርት ቤት እንደሚኖረውም አንስተዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ በዘጠኝ ዓመታት በ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ይገነባል ነው ያሉት። ከተማ አሥተዳደሩንም አመስግነዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሆስፒታል በመገንባት ሃይማኖት ሳይለዩ ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የሚሠሩ አባቶችን ማገዝ ሕዝብን እና ሀገርን መጥቀም ነው ብለዋል። መንግሥት እና ሃይማኖቶች ለሕዝብ ጥቅም በጋራ እንደሚሠሩ ማሳያ መኾኑንም ጠቁመዋል። የሃይማኖት አባቶች የመንግሥት እና የሕዝብን ሸክም ለማቅለል በመሥራታቸው ሊመሠገኑ እንደሚገባም ገልጸዋል። ሁሉም ሃይማኖቶች የሀገርን ሰላም እና አንድነት ለማስቀጠል፣ ትውልድን ለመገንባት ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አባቶቹን የሚመስል ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል። የሚገነባው የሆስፒታል መንደር በመኾኑ በቀጣይም ማስፋፊያ ቦታ ይሰጣል ነው ያሉት።

እንዲህ ዓይነት መልካም ተግባር የሚፈጽሙ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትንም ለማገዝ ከተማ አሥተዳደሩ ዝግጁ ነው ብለዋል።

​#አሚኮ_ዜና #መሠረተ_ልማት #ባሕርዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#AmharaMediaCorporation #BahirDar #Ethiopia #Infrastructure #Healthcare #HospitalConstruction #AmharaRegion
#ባሕር_ዳር #ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 3ኛውን ሀገራዊ “የጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ ንቅናቄ” አስጀመሩ።
Next articleበሐረሪ ክልል በሙሉ ድምፅ የጸደቀው እና ወደ ምክር ቤት የተመራው ረቂቅ በጀት! ✨🏛️