የሕጻናት እና የሴቶች ደኅንነት መጠበቅ የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን ይገባል።

7

 

#ባሕር_ዳር፡ ሰኔ 27/2018 ዓ.ም
የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕጻናት ጥበቃ እና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ምላሽ አሰጣጥ ክላስተር ጋር ዓመታዊ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው የሕጻናትን መብት ለማስጠበቅ እና የሴቶችን ጥቃት በመከላከል ዙሪያ የተከናወኑትን ተግባራት ዓመታዊ አፈጻጸም በመገምገም የተሻለ አሠራርን መዘርጋት እና የተቋማትን አቅም ለማጠናከር ታልሞ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በጦርነት እና ግጭቶች ምክንያት የተጎዱ ሕጻናትን ጥበቃ ማረጋገጥ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የፆታ፣ የሥነ-ልቦና እና ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት በጋራ ሢሠራ መቆየቱን አውስተዋል።

ከግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ባለፈ በጊዜያዊ እና በቋሚነት ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። በዚህም ለውጦች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ጭምር መከላከል እንደሚገባም ገልጸዋል።

በክልሉ ከ1 ሚሊዮን በላይ የብዙዎችን ምላሽ የሚሹ ሕጻናት መኖራቸውን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት እንዲሁም የሲቪክ ማኅረሰብ ድርጅቶች ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኤስ.ኦ.ኤስ የሕጻናት መንደር በኢትዮጵያ የአማራ ክልል ኘሮግራም ዳይሬክተር መሠረት ግዛቸው ድርጅቱ ሕጻናትን በሁለንተናዊ መልኩ በመደገፍ፣ በተለይም ወላጅ አልባ ሕጻናትን አሳድጎ ለቁም ነገር በማብቃት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ሕጻናትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲያድጉ ማበረታታት፣ በተለየ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከተለያዩ ደግሞ አሳዳጊዎችን በመቅጠር በልጆች ማሳደጊያ ግቢ ውስጥ እንዲያድጉ እና አምራች ዜጋ እንዲኾኑ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች እና ሕጻናት ማኅበራት ኅብረት የፆታዊ ጥቃት ጥበቃ እና ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ሜሮን ዓለማየሁ ኅብረቱ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል እና ለጥቃቱ ሰለባዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም የገንዘብ ድጋፍ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማቅረብ እና የሥነ ልቦና ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።

የሴቶችን ጥቃት መከላከል እና የሕጻናት ደኅንነት መጠበቅ ላይ የጋራ ኀላፊነት በመኾኑ ሁሉም ተቀናጅቶ በመሥራት ችግሩን መቀነስ ወሳኝ መኾኑም ተመላክቷል።

#አሚኮ_ዜና #ባሕር_ዳር #የኮሪደር_ልማት / #CorridorDevelopment

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleባሕር ዳር 🌴 በከተሞች የኮሪደር ልማት ትግበራ አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች 🏙️
Next articleየፍኖተ ሰላም መምህራን ኮሌጅ ተመራቂዎች አዲስ ምዕራፍ! 🎓 📜