🇪🇹የኢትዮጵያን ገጠራማ ሥፍራ የማዘመን ጉዞ

23

 

#ባሕር_ዳር: ሰኔ 27/2018 ዓ.ም
🏡የገጠር ኮሪደር ልማት በኢትዮጵያ የገጠሩን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ የተጀመረ ሀገራዊ የልማት መርሐ ግብር ነው፡፡

በከተሞች የታየውን ውጤታማ የኮሪደር ተሞክሮ ወደ ገጠሩ ማኅበረሰብ በማስፋፋት፣ የእያንዳንዱን አርሶ አደር ቤት፣ ግቢ እና አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ ማዘመን ላይ ያተኮረ ነው። መርሐ ግብሩ ከተጀመረ ጀምሮ በርካታ ሞዴል መንደሮች ተመርቀው ወደ ሥራ ገብተዋል።

ከወራት በፊት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሳይናሳቢያ ቀበሌ የተጀመረውን ሞዴል የገጠር ኮሪደር መርቀው ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት የገጠሩን ማኅበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር ታስቦ የተጀመረ መርሐ ግብር ነው።

ሥራው በገጠሩ ማኅበረሰብ ዘንድ የተለመደው ሰው እና ከብት በአንድ ላይ የሚኖርበትን ልማድ የሚቀይር መኾኑን ገልጸዋል።

የከተማ ኮሪደር ከተሞችን ውብ እና ማራኪ እንዳደረጋቸው ሁሉ የገጠር ኮሪደርም የአርሶ አደሩን አካባቢ ውብ በማድረግ በቀላል የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖሩ ያስችላል ነው ያሉት።

የመብራት፣ የውኃ፣ የሕክምና አገልግሎት፣ ትምህርት ቤት እና ሌሎችንም መሠረተ ልማቶችን በተማከለ መንገድ ለማግኘት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል። ሁሉም ባለው አቅም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።

በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሳይናሳብያ ቀበሌ የገጠር ኮሪደር ተጠቃሚ ነዋሪዎችም የኮሪደር ልማት በከተማ እንጂ በገጠር ሰምተው እንደማያውቁ እና መንግሥት በቅርቡ በጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት ተጠቃሚ በመኾናቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የተሠራው ቤት ሎጅ እንጂ የግለሰብ ቤት አይመስለንም በማለት ያላቸውን ስሜትም ገልጸውልናል። የተሻለ ኑሮ ለመኖር አዲስ ተስፋ እንዳጎናጸፋቸውም ይገልጻሉ።

ከአሁን በፊት ይኖሩት ከነበረው ዘልማዳዊ አኗኗር ወደ ዘመናዊ አኗኗር የሚያሸጋግር እንደኾነም ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።

#አሚኮ #የገጠር_ኮሪደር #ኢትዮጵያ #RuralCorridorDevelopment #RuralModernization

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር! 🚀
Next articleየገጠር ኮሪደር ልማት ለአርሶ አደሩ ሁለንተናዊ የኑሮ ሽግግር 🚜🏡