
ባሕር_ዳር: ሰኔ 26/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ እና የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ “ዘመናዊ ግብርና ለሁለንተናዊ ልዕልዕና” በሚል መሪ መልዕክት ከምዕራብ አማራ የግብርና እና የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ባለሙያዎች እና ኀላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ክልሉ የተለያዩ የተፈጥሮ ጸጋዎች እንዳሉት ገልጸዋል። ጸጋዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉት በአንድነት እና በቅንጅት መሥራት ሲቻል በመኾኑ በአንድነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
“ግብርና የኢኮኖሚ ሞተር ነው” ያሉት ኀላፊው ታሪካዊ ኀላፊነትን ለመወጣት ታታሪነትን፣ ቁርጠኝነትን የሕዝብ አገልጋይነትን በአንድነት መንፈስ መፈጸም እንደሚገባም አንስተዋል።
👉 ግብርና ቢሮ በበጀት ዓመቱ ምን ተገበረ?
በበጀት ዓመቱ በመስኖ ልማት ከ319 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለምቷል። 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል።
በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማትም ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ግብርናን በቴክኖሎጅ በማገዝ ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ውይይት እንደሚደረግ አንስተዋል። በቀጣይ ወራት በትኩረት በመሥራት ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
👉በቀጣይ ምን ታቅዷል?
በ2018/19 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይለማል ብለዋል። 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃልም ነው ያሉት።
3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እንደሚለማ የተናገሩት ኀላፊው 1ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተር እርሻ ይታረሳል ብለዋል።
የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) ውይይቱ ያለፉት ዓመታት ሥራዎችን በመገምገም፤ መልካም ተግባራትን በማስቀጠል እና ክፍተቶችን በማረም ይበልጥ ውጤታማ ለመኾን የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ተስፋ ሰጭ የሌማት ትሩፋት ሥራ መከናወኑን አንስተዋል። በክህሎት ላይ የተመሠረተ ሥራን በቀጣይ በጀት ዓመት ለመፈጸም ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት።
የሁለቱ ቢሮዎች ቅንጅት እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ውጤታማ ሥራ እንዲፈጥሩ ያደርጋል ብለዋል።
የክልሉ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና እና የእንስሳት ሃብት ልማት መኾኑን ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ባለሙያዎች በጸጥታ ፈተና ውስጥ በማለፍ የግብርና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየሠሩ በመኾናቸው አመስግነዋል።
ግብርና በአየር ንብረት ለውጥ የሚፈተን በመኾኑ ፈተናዎች ይበዙበታል ያሉት አስተባባሪው በተፈጥሮ የሚራቆቱ መሬቶችን መልሶ አለማቋቋም ችግር እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ለአርሶ አደሮች ቴክኖሎጅን በማላመድ ግብርናን ልናዘምን ይገባል ነው ያሉት።
#አሚኮ-ዜና#ግብርና#አማራ-ክልል#ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
