💎 የማዕድን ሃብት ከጥሬ ዕቃ ወደ እሴት ጭማሪ

6

 

​#ባሕር_ዳር: ሰኔ 26/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል የተለያዩ የማዕድን ክምችትን የያዘ ነው። ይህም ለክልሉ እና ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አቅም ያለው የሃብት ማዕከል ያደርገዋል። ከእነዚህም መካከል በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ የኾኑት የኦፓል እና የወርቅ ሃብቶች ይገኙበታል።

በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ አሥተዳደር ቡድን መሪ በሪሁን አበረ በወረዳው ወጣቶች በማኅበራት ተደራጅተው ኦፓል እያመረቱ እንደኾነ ገልጸዋል።

ማዕድኑን ከመሬት ካወጡ በኋላ ወደ ገበያ ከማቅረባቸው በፊት አፈር የማራገፍ ሥራ እና የመቁረጥ የመጀመሪያ ደረጃ የእሴት ጭማሪ ሥራዎችን እያከናወኑ መኾኑን ነግረውናል። ይሁን እንጂ አምራቾች ማዕድኑን ይበልጥ ተፈላጊ ወደኾኑ ምርቶች በመቀየር ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ተጨማሪ ሙያዊ ሥልጠናዎች እንደሚያስፈልጓቸው ነው የጠቆሙት።

​💰📊 የደቡብ ወሎ ዞን ማዕድን ሃብት ልማት መምሪያ ኅላፊ አሕመድ አበባው በዞኑ የሚገኘውን ሰፊ የማዕድን ሃብት እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ3 ሺህ 500 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት። ከ300 በላይ የሚኾኑ ኢንተርፕራይዞች በመደራጀት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል።

እንደ ዞን በማዕድን ሃብቱ በሀገር ውስጥ ገበያ 20 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል። የተሻለ ምንዛሬ መገኘቱንም ተናግረዋል።

🌍 የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዝናው አበበ በክልሉ በርካታ ማዕድናት መኖራቸውን ገልጸዋል። ማዕድናት ያለ ምንም ተጨማሪ እሴት ከክልሉ እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነውም ብለዋል። በዚህም ግራናይት እና ሌሎች ማዕድናት እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ገበያ ይቀርባሉ ነው ያሉት።

​ሕገ ወጥ የደላሎች ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስ አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ ለባለሀብቶች የሚያቀርቡበት የግብይት ሥርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት። በተለይም ኦፓል እና ወርቅ ማዕድናት ላይ የገበያ ትስስር መዘርጋቱን ነው የተናገሩት።

የማዕድን ሃብቱን ቴክኖሎጂ እና ዕውቀት በመጨመር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

#የማዕድን_ሀብት #ኦፓል #የወርቅ_ማዕድን #የእሴት_ጭማሪ #MineralWealth #OpalMining #GoldMining #ValueAddition

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌿💵✨ የቱሪዝሙ አዲስ ኅይል
Next article“ለአርሶ አደሮች ቴክኖሎጅን በማላመድ ግብርናን ልናዘምን ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)