🌿💵✨ የቱሪዝሙ አዲስ ኅይል

4

 

#ባሕር_ዳር: ሰኔ 26/2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ ልዩ የኾኑ መልከዓ ምድራዊ ገጽታዎች፣ ታሪክ፣ አርኪዮሎጂ እና ሕያው የባሕል ቱሪዝም መስህቦች አሏት። የሃይማኖት በዓላትን፣ ታሪካዊ ቦታዎችን እና ብሔራዊ ፓርኮችን ጨምሮ በተለያዩ መስህቦች የምትታወቅ ተወዳጅ የቱሪስት መዳረሻም ናት።

የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የነጃሽ መስጊድ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጥንቷ የአክሱም ከተማ ተወዳጅ ታሪካዊ ቦታዎች ናቸው። የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች፣ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ የደናክል ዝቅተኛ ቦታ እና ዳሎል በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ናቸው።

የሰሜን ተራራዎች፣ የትግራይ ገራልታ ተራራዎች እና የባሌ ተራራዎሽ በጉዞ አድራጊዎች ዘንድ በሚገባ የታወቁ ናቸው። በሁሉም ዓይነት መልክ እና ዝርያ የሚገኙ አዕዋፋት እና የዱር እንስሳት መገኛም ናት።

በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሱካንታ ሳርካር (ዶ.ር) የተሠራው ጥናት ኢትዮጵያ ለዱር እንስሳት ቱሪዝም፣ ለቅርስ ቱሪዝም፣ ለገጠር ቱሪዝም፣ ለባሕል ቱሪዝም እና ለግብርና ቱሪዝም በርካታ ዕድሎች አሏት ይላል። ይሁን እንጂ በቅንጅት እና በፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ፣ በደካማ ማስተዋወቅ፣ በሠለጠነ የሰው ኅይል እጥረት እና በቱሪስት መገልገያ ተቋማት እጥረት ግን ከዘርፉ የሚጠበቀውን ሳታገኝ ቆይታለች።

ጥናቱ የቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከመክፈት እና ካለመክፈት፣ ተጨማሪ የመስህብ ስፍራዎችን ከማቅረብ፣ ጎብኝዎች የራሳቸውን እሴት እና ተሳትፎ የሚያክሉበትን ዕድል ከማመቻቸት፣ ለውጥ አምጭ የኾኑ አዳዲስ አሠራሮችን ከመተግበር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መኾኑንም አስምሮበታል።

ኢትዮጵያ ዛሬ በታሪካዊ ቅርሶቿ ላይ ብቻ ከተመረኮዘ ቱሪዝም ወጥታ የኮሪደር ልማት እና የአረንጓዴ አሻራን በማቀናጀት አዳዲስ ማራኪ መዳረሻዎችን እያለማች የምትገኘውም ለዚሁ ነው።

በአረንጓዴ አሻራ የተራቆተው ደን ወደነበረበት ሲመለስ፣ ምንጮች ሲፈልቁ የደን ማደሪያ አጥተው የተሰደዱ የዱር እንስሳት እና አዕዋፋት ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ፤ ይህም ተጨማሪ የመስህብ ሀብት ኾኖ መዳረሻን ያሰፋል፤ ለዘርፉ ተጠባቂ የገቢ አቅምም ይኾናል።

አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ተፈጥሮዋን የምትንከባከብ ጽዱ እና አረንጓዴ ሀገር የሚል አዲስ ገጽታም አላብሷታል። የገበታ ፕሮጀክቶች ይህንን አረንጓዴ ገጽታ ተላብሰው መሠራታቸው የቱሪዝሙን ኢንዱስትሪ ቀጣይነት ያረጋግጣል።

ነባር ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ከእነዚህ አዳዲስ ልማቶች ጋር ተቀናጅተው ቱሪዝምን የጋራ ማንነት መገለጫ እና የሀገራዊ አንድነት ግንባታ መሠረት አድርገውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ነባር ቅርሶችን ከማደስ በተጨማሪ በገበታ ፕሮጀክቶች እየለሙ የሚገኙ አዳዲስ አካባቢዎች የቱሪዝም ዘርፉን የስበት ማዕከልነት እየጨመሩት ነው ብለዋል። በዚህ ዓመትም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን በመቀበል ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴውም ጨምሯል። ከ50 ነጥብ 16 ሚሊዮን በላይ በሚኾኑ ኢትዮጵያውያን ተንቀሳቅሰው ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

የቱሪስት መዳረሻዎች ብቻቸውን በቂ ባለመኾናቸው የማረፊያ ቦታዎች፣ የትራንስፖርት እና የዲጂታል አገልግሎቶች ከልማቱ ጋር ተናበው እየተሠሩ ነው ብለዋል።

#አሚኮ_ዜና #ቱሪዝም #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleውሸት ዓለምን እየፈተነ ያለበት ጊዜ ላይ ነን!