በአማራ ክልል የንጹሕ መጠጥ ውኃ ሽፋን 79 ነጥብ 91 በመቶ ደርሷል።

3

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ በክልሉ የንጹሕ መጠጥ ውኃን ተደራሽ በማድረግ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል።

የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኅላፊ ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) በክልሉ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ሽፋኑን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም በክልሉ ባለፉት 11 ወራት በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

​✅ በገጠሩ አካባቢ ባለፉት 11 ወራት የተሠሩ ሥራዎች፦

👉 2 ሺህ 445 አነስተኛ የውኃ ተቋማት ለመገንባት ታቅዶ 2 ሺህ 663 አነስተኛ የውኃ ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

👉 25 መካከለኛ እና ከፍተኛ የውኃ ተቋማት ለመገንባት ታቅዶ 14 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀዋል።

👉 በክልሉ የገጠራማ አካባቢዎች የውኃ ሽፋን ከነበረበት 76 ነጥብ 89 በመቶ ወደ 79 ነጥብ 66 በመቶ ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል።

ከ513 ሺህ 300 በላይ ማኅበረሰቦችን በገጠር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

​✅ በ11 ወሩ በክልሉ የከተማ አካባቢዎች የተሠሩ ተግባራት፦

✍️13 መካከለኛ እና ከፍተኛ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀዋል።

✍️ የከተማ የውኃ ሽፋን ከ78 ነጥብ 04 በመቶ ወደ 80 ነጥብ 34 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል።

✍️ ​ከ130 ሺህ በላይ የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አንስተዋል። የንጹሕ መጠጥ ውኃን በፍትሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።

​✅ ብልሽት የሚያጋጥማቸውን የወኃ ተቋማት ጥገና በማድረግ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ 17 ሺህ 207 የሚኾኑ የውኃ ተቋማትን ለመጠገን ታቅዶ 24 ሺህ 312 የሚኾኑትን ከቀላል እስከ ከባድ ጥገና ተደርጓል ብለዋል። በዚህም የብልሽት ምጣኔን በ2 ነጥብ 67 መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።

በገጠር እና በከተማ የነበረው የክልሉን አጠቃላይ የውኃ ሽፋን ከ77 ነጥብ 25 በመቶ ወደ 79 ነጥብ 91 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል። በዘርፉ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው​

#አማራክልል #ንጹሕውኃ #ውኃእናኢነርጂ #AmharaRegion #CleanWater

Previous articleበምራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ባደረገው ኦፕሬሽን 116 ጽንፈኞችን መደምሰሱን ምሥራቅ እዝ አስታወቀ።
Next articleየሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዋና የሂደት መገለጫዎች!