
ሰቆጣ: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለአዲሱ የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ ከሚያስገነባቸው ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው። በወለህ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ይህ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ እየተከናወነ ነው ። ግንባታውን በሁለት የኮንስትራክሽኖች ድርጅቶች እየተሳለጠ ይገኛል።
ትምህርት ቤቱ ለመጭው የ2019 የትምህርት ዘመን ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰይፈ ሞገስ ናቸው።
የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ ባሻገር የዋግ ኽምራን ትምህርት ቤቶች ተወዳዳሪ እና ተፎካካሪ እንዲኾኑ ያደርጋል ብለዋል ኀላፊው። አዳሪ ትምህርት ቤቱ ሲጠናቀቅ ከ600 በላይ ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።
በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ትምህርት መምሪያው ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
አዳሪ ትምህርት ቤቱን እየገነባ የሚገኘው የመካሻ አምባ ኮንስትራክሽን ምክትል ሥራ አሥኪያጅ አዳነ ወርቁ አዳሪ ትምህርት ቤቱን ካለበት ደረጃ ለማድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳለፉ አስታውሰዋል።
ሀገርን እና ትውልድን የሚገነባውን ትምህርት ቤት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አስፈላጊ ጥሬ እቃዎቸ ገብተው የማጠቃለያ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ነው የገለጹት። እስከ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ እየሠሩ መኾኑንም ሥራ አሥኪያጁ አብራርተዋል።
የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት አማካይ የግንባታ አፈጻጸም 80 በመቶ መድረሱን ከተቆጣጣሪ መሃንዲሶች የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
