
አዲስ አበባ: ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የክረምት የጽዳት ንቅናቄ እና የበጎ ፈቃድ ሥራን አስጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የክረምት ወራትን ተከትሎ በከተማዋ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ቀድሞ ለመከላከል እና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ሥርዓትን ለመተግበር የሚያስችል የክረምት የበጎ ፈቃድ እና የጽዳት ንቅናቄ መርሐግብርን ነው ያስጀመረው።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአዲስ አበባ ተግባራዊ እየኾነ ያለው የክረምት የጽዳት ንቅናቄ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ከቁሳዊ ድጋፍ ባለፈ የሰውን አቅም የመገንባት እና የባለቤትነት ስሜትን የማሳደግ ትልቅ አቅም መኾኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የሚተገበሩት የክረምት ጽዳትም ኾነ የበጎ አድራጎት ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሕል እየኾኑ እና በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድም ከፍተኛ አድናቆትን እያተረፉ ይገኛሉ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህ እንቅስቃሴ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪውን ማኅበራዊ ትስስር በማጠናከር እና ለከተማዋ ያላቸውን የባለቤትነት ስሜት በእጅጉ በማሳደግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ዛሬ የተጀመረው የጽዳት ንቅናቄ በየአካባቢው የሚጣሉ ደረቅ ቆሻሻዎች የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮችን እና ቱቦዎችን በመዝጋት ለጎርፍ አደጋ መንስኤ እንዳይኾኑ ለመከላከል እና ኅብረተሰቡ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ በመለየት ወደ ሀብት እና የሥራ ዕድል መቀየር የሚቻልበትን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ እንደኾነ ተናግረዋል።
ከንቲባ አዳነች ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የከተማዋን የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች፣ ድልድዮች እና የወንዝ ዳርቻዎችን ከደረቅ ቆሻሻ የማጽዳት ሥራ በከፍተኛ ትኩረት እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #የአካባቢ_ጽዳት_ዘመቻ #አዲስ_አበባ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
