
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2018/19 የመኸር እርሻ 5 ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በማረስ 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል።
የምዕራብ ጎጃም ዞንም ለመኸር እርሻ ሥራ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፤ አርሶ አደሮችም የዘር ሥራ ውስጥ ናቸው።
አርሶ አደር በድሉ ስንታየሁ በአካባቢያቸው የሰፈነውን ሰላም እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም መሬታቸውን በበቆሎ ዘር እየሸፈኑ ነው አሚኮ ያገኛቸው። ምርታማነታቸውን ለማረጋገጥም ምርጥ ዘርን እየተጠቀሙ ነው።
የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው በተቻለ መጠን የተፈጥሮ ማዳበሪያን እየተጠቀሙ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሰውመኾን ተገኘ እንዳሉት በዞኑ በመኽር ወቅት ብቻ 226 ሺህ 597 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለመሸፈን ታቅዷል፤ ከዚህም 14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
ለዕቅዱ መሳካትም 1 ነጥብ 16 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል። እስካሁን ከቀረበው 703 ሺህ ኩንታል ውስጥ 325 ሺህ ኩንታሉ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል።
38 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለማሰራጨትም ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ 13 ሺህ ኩንታሉ ተሰራጭቷል።
አርሶ አደሮቹ ያነሱት የማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪ ምክንያቱ ዓለም አቀፉ ገበያ መኾኑን አንስተዋል። ዋጋው ከዚህም በላይ እንዳይንር በማሰብ በመንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ተደርጎበት እየቀረበ መኾኑንም ተናግረዋል።
በአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ውድነት ምክንያት ምርታማነት እንዳይቀንስ የብድር አማራጮች መመቻቸታቸውን እና ብድር የሚያስፈልጋቸውን አርሶ አደሮች የመለየት እና የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #ግብርና #ምዕራብ_ጎጃም #ፍኖተሰላም #ኢትዮጵያ🇪🇹
ዘጋቢ ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
