
ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፅናት፣ ጠንካራ ሥራ እና ተስፋ አለመቁረጥ ሰውን ካለበት ውድቀት አንስተው ወደ ላቀ ስኬት እንደሚያደርሱት በባሕር ዳር ከተማ በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማራው ወጣት በረከት ይበልጤ አንዱ ሕያው ምስክር ነው። በአንድ ወቅት የነበረውን ሀብት ሁሉ አጥቶ ከዜሮ የተነሳው በረከት፣ ዛሬ ላይ የተሳካለት የዶሮ አርቢ እና የታክሲ ባለንብረት ለመኾን በቅቷል።
👉ከከባድ ስብራት ወደ አዲስ ተስፋ
ወጣት በረከት ይበልጤ ቀደም ሲል የተሽከርካሪ ባለቤት እና ጥሩ ኑሮ የነበረው ቢኾንም በአጋጠመው አጋጣሚ ግን ሁሉንም ሀብቱን በአንድ ጊዜ አጥቶ ለከባድ የሥነልቦና ስብራት ተዳርጎ ነበር። “አለን ብለን የምንመካበት ሀብት ጠፊ ነው” የሚለው በረከት፣ ወደመንፈሳዊ ቦታዎች በመሄድ ራሱን ካረጋጋ በኋላ በ2013 ዓ.ም ሕይወቱን በአዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ወሰነ።
👉በ280 ብር የተጠነሰሰው ትልቅ ስኬት
ለዛሬው ስኬቱ መነሻ የኾነችው እናቱ ተበድራ የሰጠችው 280 ብር ብቻ ነበረች። ወጣት በረከት ሥራውን ለመጀመር እና ለማሳደግ የከፈለውን መሥዋዕትነት ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦
👉የቤት ኪራይ ወጭን ለመቆጠብ ረጅም ጊዜ ዶሮ ቤት አድር ነበር።
👉ከአንድ እንቁላል አንድ ብር አትርፎ ለመሸጥ ሲል፣ በርካታ እንቁላሎችን በትክሻው ተሸክሞ ረጅም ርቀት ይጓዝ ነበር።
👉አሁናዊ የገቢ መጠን እና የሥራ ዕድል ፈጠራ
✍በብርቱ ትግል እና በከፍተኛ ፅናት የተጀመረው የዶሮ እርባታ ሥራ፣ በአሁኑ ወቅት የወጣቱን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።
✍በአሁኑ ወቅት ከ1ሺህ 200 በላይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች አሉት።
✍ከእንቁላል ሽያጭ በወር 90 ሺህ ብር የሚያገኝ ሲኾን፣ ለዶሮ ቤት ኪራይ 30 ሺህ ብር ከፍሎ በቀን 3ሺህ ብር የተጣራ ገቢ ያገኛል።
✍በዚህ ሥራ ባገኘው ገቢ በአንድ ወቅት ያጣውን ሀብት በመተካት የታክሲ ባለንብረት ለመኾን የበቃ ሲኾን፣ ከራሱ አልፎ ለአራት ወጣቶችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
“በስኬት መሐል ብዙ ፈተናዎች አሉ፤ እኔ ግን ነገን በተስፋ ሰንቄ በመሥራቴ ችግሮችን በፅናት ተሻግሬአለሁ” ይላል በረከት ይበልጤ
ወጣቱ አክሎም በቀጣይ ከኪራይ ነፃ የኾነ የመሥሪያ ቦታ ቢመቻችለት ሥራውን ይበልጥ አስፋፍቶ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ሕልም እንዳለው ገልጿል።
#አሚኮ_ዜና #ስኬት_ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ማማነሽ ገኔ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
