
እንጅባራ፡ ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 447ኛው የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቻግኒ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይበልጣል ሰይድ አረፋ የነብዩ ኢብራሒም እና የልጃቸው የነብዩ እስማኤል ታዛዥነት፣ ፅናት እና የመስዕዋትነት ታሪክ የሚዘከርበት ታላቅ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉን በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በወንድማማችነት እና የተቸገሩትን በመደገፍ ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላም የሚያደርገውን ትጋት እና ጸሎት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አንስተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ኡመር ሙሐመድ በዓሉ ወንድማችነት፣ መከባበር እና መደጋፍ ጎልቶ የሚታይበት ታላቅ የበረከት በዓል መኾኑን ተናግረዋል።
በዓሉን ሃይማኖቱ በሚያዝዘው መሠረት ያለው ለሌለው በማካፈል፣ አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ እና በመደገፍ ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ ውስጣዊ አንድነቱን በመጠበቅ በሀገር ግንባታ ሂደት ያለውን አበርክቶ አጠናክሮ መቀጠል ይገባልም ነው ያሉት።
#አሚኮ #እንጅባራ #ኢድአልአደሃ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
