🕋 “የፅድቋ ከተማ መካ”

4

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ቅድስት ከተማ ተብላ ትጠራለች። የሃይማኖት፣ የታሪክ እና የባሕል አምባም ናት። በመላው ዓለም ለሚገኘው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ማኅበረሰብ የመጀመሪያዋ እና እጅግ ቅድስቷ ከተማ ናት መካ።

ቅድስቲቷ መካ ከተማ መገኛዋ በሳዑዲ አረቢያ በስተምዕራብ ሂጃዝ በሚባለው ክልል ነው። ታሪኳ ደግሞ ከጥንታውያን ነብያት ታሪክ እና ከአረብ ምድር በተለይም ከየመን ሰዎች የንግድ እንቅስቃሴ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መኾኑ የታሪክ መዛግብት እና የሃይማኖቱ አባቶች ይናገራሉ።

የአማራ ክልል እስልምና ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ኢብራሂም መካ ሲነሳ ተያይዘው የሚነሱት ነብዩ ኢብራሂም ናቸው ብለዋል።

ሼህ መሐመድ ሾለ መካ ከተማ አመሠራረት ሲናገሩ ነብዩ ኢብራሂም ከተወለዱበት ኢራቅ በሕዝብ ጫና ወደ ሻም ወይም አሁን መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ሚባለው ሀገር በተሰደዱ ጊዜ ሁለተኛ ሚስት አግብተው “እስማኤልን” እንደወለዱ ተናግረዋል።

የእስማኤል እናት አራስ እንደኾነች በአሏህ ፈቃድ በዚያ ትቆይ ተብለው ብቻዋን በዚያ ቦታ ስትቆይ አሁን “ካዕባ” የሚባለው እና ትልቁ አራት ማዕዘን መስጊድ ካለበት ቦታ ላይ አዲስ ውኃ እንደፈለቀ ያነሳሉ።

አካባቢው ከዚያ በፊት ምንም ያልነበረበት ነበር ያሉት ሼህ መሐመድ ከየመን በኩል የመጡ ጎሳዎች በዚያ ሲያልፉ አይተውት የማያውቁት የወፎች ግርግር ተመለከቱ። እዚህ ቦታ አዲስ ውኃ ፈልቋል ብለው ሲሄዱም የእስማኤልን እናት አገኟት። ከዚያም ውኃ ስጭን ሲሏት ውኃ ለመስጠት በአቻ ስንቅ ያስፈልገኛል ስትላቸው በዚህ ሂደት መግባባት ችለዋል ይላሉ።

የመኖቹ ድጋሜ በዚያ ሲመላለሱ ይቺ ውኃ ካለችማ እዚህ ቦታ ሀገር መመሥረት አለብን ብለው “መካን” መሠረቱ በማለት ስለአመሠራረቷ አስረድተውናል።

በዚያ የተወለደው እስማኤል ካደገ በኋላም ነብዩ ኢብራሂም ከዚያ ቦታ ላይ “ካዕባ ወይም አራት ማዕዘኗን መስጊድ” እንደገነቡ ይገልጻሉ። በዚያ ዘመን በምድር ላይ ለአምልኮ የተመሠረተው ብቸኛው መስጊድም ያ ነበር ብለዋል።

ነብዩ ኢብራሂም መስጊዱን ገንብተው ከጨረሱ በኃላ መላው የሰው ልጅ ወደዚያ ሐጂ እንዲያደርግ አዋጅ ማስነገራቸውንም ነው የተናገሩት። ከዚያ ዕለት ጀምሮ የሐጂ ሥነ ሥርዓት በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ግዴታ ኾኖ መካሄድ እንደጀመረ አስረድተዋል።

ከዚያም ነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ጨምሮ ተካታዮቹ ነብያት የሚታደሰውን የካዕባ ክፍል እያደሱ ሥነ ሥርዓቱን አስቀጥለውታል ነው ያሉት።

በእስልምና ሃይማኖት አምስት እስላማዊ ግዴታዎች አሉ ያሉት ሼህ መሐመድ ወደ መካ የሐጂ ሥነ ሥርዓት ማድረግ አንደኛው መኾኑን አንስተዋል። ደጋግሞ ሐጂ ማድረግ ትርፍ ጽድቅ ቢያስገኝም አቅሙ የፈቀደለት ኢስላም በዘመኑ አንድ ጊዜ ሐጅ የማድረግ ግዴታ አለበት ነው ያሉት።

ወደ መካ ሐጅ ማድረግ ግዴታ እንደኾነው ኹሉ በአሏህ ዘንድ ልዩ ፅድቅ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል። በዚህ የተነሳም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ “መካ የፅድቅ ከተማ ናት” ነው ያሉት።

#አሚኮ_ዜና #ዒድ_አልአደሃ #አረፋ_በዓል #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየኢድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓል በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
Next articleየዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሀረር ከተማ እየተከበረ ነው።