“ብልጽግና በተቋማዊ እና ሕዝባዊ ባሕል ላይ በመቆም ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንክሮ የሚሠራ ፓርቲ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

6
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡ ለፓርቲው ያሳየውን ድጋፍ እና የምርጫ ቅስቀሳ አስመልክተው የምስጋና መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ሙሉ መልእክታቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በዛሬዉ ዕለት እና ባለፉት ተከታታይ ቀናት በክልላችን ሁሉም አካባቢዎች ለፓርቲችን ብልጽግና የተካሄዱ ደማቅ እና ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፎች የሕዝባችን አይነተ ብዙ ድጋፍ እና ያልተገደበ አጋርነት ያየንበት ነው።
የተደረጉት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን፤ ፓርቲያችንም ቅቡልነት አግኝቶ በአሸናፊነት እንዲያጠናቅቅ እንዲሁም የፓርቲያችን መንታ ግቦች እንዲሳኩ በማድረግ ረገድ የማይተካና እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸዉ ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፎች ናቸዉ ፡፡
ፓርቲያችን ብልጽግና በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ በእጅጉ የጨመረውን የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና የሕዝባችንን እምቅ አቅም በዉል የተገነዘበ፣ ባለፉት የለዉጥ ዓመታትም በኢትዮጵያ በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሁለንተናዊ ዉጤት እንዲመጣ ሕዝባችን የአንበሳዉን ድርሻ እንዳበረከተ በፅኑ ያምናል ፡፡
ብልጽግና በተቋማዊና ሕዝባዊ ባሕል ላይ የቆመ፣ በዴሞክራሲ የበለጸገችና ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንክሮ እየሠራ የሚገኝ ፤ የፉክክርና የትብብር ዴሞክራሲን ለማጽናት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፣ የመንግሥት ሥልጣን በሕዝብ ይሁንታ እና ውክልና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ ሊገኝ እንደሚገባው ቁርጠኛ አቋም ያለዉ ፓርቲ ነዉ ፡፡
ብልጽግናን መምረጥ ኅብረ ብሔራዊነት እና አንድነትን ማጽናት ፤ ሀገርን ካልተቋጨ እና ካልተግባባ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ችግር ዉስጥ በማዉጣትና ከግጭት እና ጦርነት አዙሪት በማላቀቅ የጸና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ለመገንባት አሻራን ማሳረፍ እንዲሁም የኋላ ቀርነት እና የድህነት ታሪክን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጨትም ነው።
ለተሻለ ሀሳብ፣ ለላቀ ተግባር የቆመውን ፓርቲያችን ብልጽግናን መምረጥ እውነትን እና ዕውቀትን መምረጥ ነው። ብልጽግናን መምረጥ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማውጣት ነው፡፡
በመሆኑም የስንዴ ነዶን በመምረጥ የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ ማስቀጠል፣ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማብሰር፣ የልጆቻችንን ተስፋ ማለምለም እና ለሀገራችን የተሟላ ልዕልና ማጎልበት በመሆኑ በመጪው ግንቦት 24 ሁሉም ዜጋ ፓርቲያችንን በመምረጥ የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪዬን እያስተላለፍኩ ለእነዚህ ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፎች ስኬታማነት ሁለንተናዊ ሚና ለነበራችሁ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ፡፡
“ኢትዮጵያን ወደተምሳሌት ሀገር”
ምልክታችን የመደመር ፣ የትብብር እና የአንድነት መገለጫ የሆነው የስንዴ ነዶ ነው !
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ብልጽግና በተቋማዊ እና ሕዝባዊ ባሕል ላይ በመቆም ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንክሮ እሚሠራ ፓርቲ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next article“የብልጽግና የጠራ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ቀርፆ የልማት ሥራዎችን ሠርቷል” አቶ አየን ብርሃን