
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡ ለፓርቲው ያሳየውን ድጋፍ እና የምርጫ ቅስቀሳ አስመልክተው የምስጋና መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ሙሉ መልእክታቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በዛሬዉ ዕለት እና ባለፉት ተከታታይ ቀናት በክልላችን ሁሉም አካባቢዎች ለፓርቲችን ብልፅግና የተካሄዱ ደማቅ እና ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፎች የህዝባችን አይነተ ብዙ ድጋፍ እና ያልተገደበ አጋርነት ያየንበት ነው።
የተደረጉት ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሆን፤ ፓርቲያችንም ቅቡልነት አግኝቶ በአሸናፊነት እንዲያጠናቅቅ እንዲሁም የፓርቲያችን መንታ ግቦች እንዲሳኩ በማድረግ ረገድ የማይተካና እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸዉ ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፎች ናቸዉ ፡፡
ፓርቲያችን ብልፅግና በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ በእጅጉ የጨመረውን የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና የህዝባችንን እምቅ አቅም በዉል የተገነዘበ ፣ ባለፉት የለዉጥ ዓመታትም በኢትዮጵያ በፖለቲካዊ ፣ በማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሁለንተናዊ ዉጤት እንዲመጣ ህዝባችን የአንበሳዉን ድርሻ እንዳበረከተ በፅኑ ያምናል ፡፡
ብልፅግና በተቋማዊና ሕዝባዊ ባህል ላይ የቆመ ፣ በዴሞክራሲ የበለጸገችና ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንክሮ እየሠራ የሚገኝ ፤ የፉክክርና የትብብር ዴሞክራሲን ለማጽናት አዲስ ምእራፍ የከፈተ ፣ የመንግሥት ሥልጣን በሕዝብ ይሁንታና ውክልና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ ሊገኝ እንደሚገባው ቁርጠኛ አቋም ያለዉ ፓርቲ ነዉ ፡፡
ብልፅግናን መምረጥ ኅብረ ብሔራዊነትና አንድነትን ማጽናት ፤ ሀገርን ካልተቋጨና ካልተግባባ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ችግር ዉስጥ በማዉጣትና ከግጭት እና ጦርነት አዙሪት በማላቀቅ የጸና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ለመገንባት አሻራን ማሳረፍ እንዲሁም የኋላ ቀርነት እና የድህነት ታሪክን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጨትም ነዉ ፡፡
ለተሻለ ሀሳብ ፤ ለላቀ ተግባር የቆመዉን ፓርቲችን ብልፅግናን መምረጥ እውነትን እና እውቀትን መምረጥ ነው ፡፡ ብልፅግናን መምረጥ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማውጣት ነው ፡፡
በመሆኑም የስንዴ ነዶን በመምረጥ የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ ማስቀጠል ፣ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማብሰር ፣ የልጆቻችንን ተስፋ ማለምለም እና ለሀገራችን የተሟላ ልዕልና ማጎልበት በመሆኑ በመጪው ግንቦት 24 ሁሉም ዜጋ ፓርቲያችንን በመምረጥ የድርሻዉን እንዲያበረክት ጥሪዬን እያስተላለፍኩ ለእነዚህ ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፎች ስኬታማነት ሁለንተናዊ ሚና ለነበራችሁ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ፡፡
“ኢትዮጵያን ወደተምሳሌት ሀገር”
ምልክታችን የመደመር ፣ የትብብር እና የአንድነት መገለጫ የሆነው የስንዴ ነዶ ነው !
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
