
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተደረገው የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
ለዚህም የጸጥታ ኀይሉ ቀደም ብሎ ያደረገው ከፍተኛ የሰው ኀይል ስምሪት እና የሎጀስቲክስ ዝግጅት ቀዳሚውን ሚና እንደተጫወተ ነው የተገለጸው። የጸጥታ ኀይሉ የድጋፍ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ጥረት ማድረጉ ውጤታማ እንዳደረገውም ተጠቅሷል።
የጸጥታ ኀይሉ በብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ ሰልፍ የነበረው የዝግጁነት መንፈስ ቀጣይ ለሚደረገው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም አስተማማኝ መሠረት የጣለ እንደኾነም ተመላክቷል። ቀጣዩ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ እና ዜጎች ያለምንም ስጋት እና መሳቀቅ በነጻነት ወጥተው የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ እንዲችሉ የሰላም ጥበቃ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።
ጠቅላይ መምሪያው ሰልፉ ፍጹም ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ግንባር ቀደም ሚና ለተጫወቱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የፌዴራል እና የክልሉ ፖሊስ፣ ሌሎች የሰላም አስከባሪ አካላት እና የጸጥታ ኀይሉን ሥራ በንቃት ላገዙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ምሥጋና አቅርቧል።
ዘጋቢ፦ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
