ኢትዮ ቴሌኮም የ10 በመቶ አክሲዮን ሽያጭ ባለድርሻዎቹን ይፋ አደረገ።

15
አዲስ አበባ፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ለ132 ዓመታት በትጋት ሲያገለግል የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት ከልማት ድርጅትነት ወደ አክሲዮን ማኅበርነት ተቀይሯል።
መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ካከናወናቸው ተግባራት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ማቋቋም እንዲሁም ዜጎች በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ማስቻል ይገኝበታል።
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን መመሪያ መሠረት የመጀመሪያውን የአክሲዮን ሽያጭ በስኬት ማከናወን መቻሉን ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ባለአክሲዮኖቹ አክሲዮናቸውን በሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ እንዲያሥተዳድሩ፣ እንዲገዙ እና እንዲሸጡ ማስቻሉንም ገልጸዋል።
አጠቃላይ አክሲዮን ከገዙ 47 ሺህ 377 ዜጎች ውስጥ 95 ነጥብ 8 በመቶ የሚኾኑት የባለቤትነት ማረጋገጫ እና አክሲዮኖችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሂደታቸውን ሙሉ በሙሉ አጠናቅቀዋል ብለዋል።
እነዚህ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሂደታቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች በገንዘብ ሲሰላ 3 ነጥብ 04 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን አክሲዮኖች ባለቤት መኾናቸው መረጋገጡንም ሥራ አሥፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት የኢትዮ ቴሌኮም ባለአክሲዮኖች በኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ላይ አክሲዮናቸውን ማንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ዝግጅት እንደተደረገም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በብሔራዊ መታወቂያ መረጃ አለመሟላት ምክንያት ገና ያልተረጋገጡ 1 ሺህ 646 ባለአክሲዮኖች መረጃዎቻቸውን በአፋጣኝ እንዲያሟሉ ኩባንያው ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮኖችን ለመግዛት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን የማያሟሉ 105 ሺህ አክሲዮኖች የአክስዮን ግዢ ጥያቄ አቅራቢ የውጭ ዜጎች የከፈሉት ገንዘብ ተረጋግጦ ተመላሽ እንደሚደረግም ሥራ አሥፈጻሚዋ አረጋግጠዋል ።
ዘጋቢ: ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎችን አሳለፈ።
Next articleትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ የማጠቃለያ የምርጫ ቅስቀሳ መርሐ ግብሩን አካሄደ።