
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 55ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
ውሳኔዎቹ ቀጥሎ ቀርበዋል፦
1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው በሁለት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለአርብቶ አደር ምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ከአፍሪካ ልማት ባንክ የአርባ ስድስት ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ (46,300,000) የአሜሪካን ዶላር ብድር ስምምነት ነው፡፡ ሁለተኛው ለስድስተኛ ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር የአንድ መቶ አርባ ስድስት ሚሊዮን አንድ መቶ ሺ (146,100,000) ኤስ ዲ አር ብድር ስምምነት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ሁለቱም የብድር ስምምነቶች ከአገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ወጥቶ ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም ባለፉት አመታት በሀገራችን በርካታ የኢኮኖሚ ለውጦች የተደረጉ በመሆኑ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን ከዘመናዊ ዓለም አቀፍ ልምዶች ጋር ለማጣጣም፤ የታክስ አለመግባባቶችን በፍትሐዊነት፣ በሰላማዊ መንገድና በቅልጥፍና ለመፍታትና የተጠያቂነትና ግልጸኝነት አሰራር ለማስፈንና የታክስ ሕጎችን በተጠናከረ መልኩ ለማስፈጸም እንዲያስችል ተደርጎ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የግብርና ዘርፍን ከተለምዶአዊ አሰራር ወደ ቢዝነስ መር ሥርዓት ለማሸጋር፤ አነስተኛ አምራቾችን የገበያ የመደራደር አቅም ለማሳደግ፣ የእሴት ጭማሪና የኢንዱስትሪ ግብዓት ትስስርን ለመፍጠር፤ የተሻለ አቅም ያላቸው ወደ መካከለኛ አልሚነት የሚደርጉትን ሽግግር በሕግ ለመደገፍ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የካርበን ገበያ ስትራቴጂ ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ ለአረንጓዴ ኢንቨስትመንት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር፣ የካርበን ግብይት አሰራሮችንና ሂደቶችን በግልፅ ለመደንገግ፣ በካርቦን ፕሮጀክት አካባቢ በሚኖረው ማህበረሰብና አካባቢው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አሰራሮችን ለመዘርጋት፤ ከካርበን ንግድ የሚገኘው ገቢ በመንግስት፣ በአልሚዎች፣ በአካባቢው ማህበረሰብ እና በባለድርሻ አካላት መካከል በፍትሃዊነት የሚከፋፈልበትን አሰራር ለመዘርጋት እና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ውሎችና የገባቻቸውን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ቃል ኪዳኖች ከሌሎች ጋር በትብብር እንድትወጣ የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ የተወያየበት ሌላው አጀንዳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ሞያዊ ነፃነትን ለማረጋገጥ፣ የተቆጣጣሪ እና የፈጻሚ አካላትን የቁጥጥር እና የአሠራር ተግባራትን ሚና በግልፅ ለመለየት፣ በሁሉም ኦፊሽያል ስታቲስቲክስ አመንጪዎች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር፣ የመረጃ ምስጢራዊነትን ለመጠበቅ፣ የስታቲስቲክስ ውጤቶችን ጥራት ለማሻሻል፣ ተደራሽነታቸውን ለማረጋገጥ እና ሀገራዊ አሠራሮችን ከዓለም አቀፍ የስታቲስቲክስ መርሆዎች እና ደረጃዎች ጋር ለማጣጣም እንዲያስችል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
6.አስከትሎም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ ፖሊሲው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ከአሥር አመቱ የልማት ዕቅድ፣ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ፣ ከምዕተ አመቱ የልማት ግቦች እና ከሌሎች ፖሊሲዎች ጋር ተጣጥሞ የአገራችንን የኢነርጂ ሀብት በአነስተኛ ዋጋ በማልማት ዘላቂ፣ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ በዋጋ ተመጣጣኝና ተወዳዳሪ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲኖርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው ብሄራዊ የሴቶች ማብቃት እና የስርዓተ ጾታ እኩልነት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ ፖሊሲው ለስርአተ ጾታ መዛባት ስር ነቀል የሆኑ ጉዳዮች ላይ በቂ ትኩረት ለመስጠት፣ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን በአግባቡ ለመከላከል እና ጥበቃና ምላሽ ለመስጠት፣ ልዩ ትኩረት ለሚሹ ሴት አካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ስርአተ-ጾታን መሰረት ካደረጉ አለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች ጋር በማጣጣም ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. ቀጥሎም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢንሹራንስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ገበያውን ተኣማኒነት የሚያጠናክር፣ ፍትሃዊ፣ ደህንነቱ ተረጋገጠ እና የተረጋጋ የኢንሹራንስ ገበያ እንዲኖር የሚያበረታታ፣ የመድን ገቢዎችን እና የመድን አገናኞችን ደንበኞች ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ የኢንሹራንስ ገበያውን ለመቆጣጠርና ለመምራት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. በማስከተል ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ የንግድ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የንግድ ስርአትን በአግባቡ ለመምራት፣ በተመረጡ የገበያ ክፍተት ባለባቸው ዘርፎች ክፍተቶችን ለመሙላት የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር፣ የሀገራችንን የወጪ ንግድ በግብርና ምርቶች ያለውን ጥገኝነት በማላቀቅ የወጪ ምርትና አገልግሎት ብዝሃነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ የምርት ደህንነት መስፈርቶችን ለማውጣት እና ፍትሃዊ የንግድ አሰራርን ለመዘርጋት፣ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነትን እንዲገነቡ፣ ምርታማነትን እንዲያሳድጉና የአካባቢ አቅምን እንዲያዳብሩ ድጋፎችን በመስጠት በዘርፉ ያሉ ተግዳሮችን ለመፍታት እንዲያስችል ረቂቅ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣንን አደረጃጀት፤ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ባለስልጣኑ በህግ የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንዲያስችለው ማሻሻያ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላት ተጠቃሚ የሚሆኑ ባለቤቶችን መረጃ ግልጸኝነት ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በአግባቡ ለማስፈጸም እንዲያስችል ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ከሥርዓተ ምግብ መዛባት ጋር የተያያዙ በሽታዎች በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢያዊ፣ በምርታማነትና በማህበራዊ መስተጋብር እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቀነስና ለማጥፋት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይህን ስራ የሚያስተባብር አደረጃጀት ለመፍጠር፤ ሀብት በዘላቂነት ለመመደብና የማህበረሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ፣ ሀገራችን የገባቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶችና የተቀመጡ የምግብ ስርዓትና ሥርዓተ ምግብ ግቦችን ለማሳካት የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
1. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስት የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ አፈጻጸምን ለመደንገግ በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስት የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ በታወቀ ጥቅል የበጀት ድጋፍ ስርዓት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ፣ የፋይናንስ ተጠያቂነት፣ ፍትሃዊነት እና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ፣ የራስን ወጪ በራስ የመሸፈን ድርሻን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ፣ በተቋማቱ መካከል ተመጣጣኝ የመማር-ማስተማር፣ የአገልግሎት ጥራት እና ፍትሃዊነትን ባረጋገጠ ሁኔታ ሀላፊነት የተሞላበት ስራዎችን እንዲያከናውኑ ለማስቻል ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
