
ፍኖተሰላም: ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የድጋፍ እና የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያውን በቡሬ ከተማ አካሂዷል።
የቡሬ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሃይማኖት አሰፋ ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ፈተናዎችን አልፎ እዚህ መድረሱን አስታውሰዋል።
ፓርቲው ካለፈው ተሞክሮው በመነሳት የቆዩ አመለካከቶች እና አሠራሮችን መከለሱን፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመቅረጽ በአዲስ መነሳቱን ጠቁመዋል። በቀጣይም ፓርቲው ከሕዝብ ጋር በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መንግሥት ለመመሥረት የሕዝቡን ውሳኔ እየጠበቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አሥኪያጅ ዳኛቸው አስረስ ምርጫው ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሀገር የሚያሸንፉበት እንዲኾን መላው ሕዝብ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ምርጫ ዜጎች ፍላጎታቸውን በድምጻቸው የሚወስኑበት ዋና መሳሪያ መኾኑንም ገልጸዋል።
ፓርቲው ምርጫውን ካሸነፈ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች በማዳመጥ ምላሽ ለመስጠት እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከግብ ለማድረስ በትጋት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
ምርጫው ነጻ፣ ሰላማዊ እና ተዓማኒ እንዲኾን ሕዝቡ በምርጫው ዕለትም ኾነ ከምርጫው በኋላ ሰላማዊ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ አለሙ ምርጫ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ለመንግሥት ምስረታ አማራጭ የሌለው ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ መኾኑን አስረድተዋል። ፓርቲው የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምስረታ እና የሽግግር ፍትሕ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ፣ የባሕር በር እንዲከፈት እና ዴሞክራሲ እንዲጸና መላው ሕዝብ ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትሐዊ እንዲኾን ጥረት እንዲያደርግ እና ብልጽግናን እንዲመርጥ ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
