
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚያገለግሉ የድምፅ መስጫ ካርዶች ሕትመት ተጠናቆ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውንና ስርጭት መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ዛሬ ለጋዜጠኞች እና ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በሰጡት መግለጫ፤ ቦርዱ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እያከናወናቸው ያሉ የቅድመ-ምርጫ ዝግጅቶችንና የድምፅ መስጫ ቀንን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሰብሳቢዋ እንደገለጹት፤ ለምርጫው እጅግ አስፈላጊ የኾኑት የድምፅ መስጫ ካርዶች የሕትመት ሥራቸው ተጠናቆ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር በተያያዘም፣ ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ቦርዱ ባበለጸገው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መተግበሪያ (Application) አማካኝነት የዕጩዎች ምዝገባ ሲከናወን መቆየቱን ሰብሳቢዋ አስረድተዋል።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ግልጽ እንዲሆን ለማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውንና ፕሮግራሞቻቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁባቸው 19 የክርክር መድረኮች መዘጋጀታቸውንም ቦርዱ በመግለጫው ይፋ አድርጓል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ-ምርጫ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀጣይ ሂደቶችን በተመለከተም ለሕዝብ መረጃ መስጠቱን እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
