
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እና የምርጫ ቅስቀሳ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ባሕር ዳር ከተማ ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረች እና በተፈጥሮ የተዋበች ከተማ ብትኾንም ዐይን ገላጭ እና ግዙፍ የኾኑ ፕሮጀክቶች የተሠሩላት ግን በብልጽግና ፓርቲ ነው ብለዋል።
ከተከናወኑ ትልልቅ የልማት ሥራዎች ውስጥም በዓባይ ወንዝ ላይ የተሠራውን ድልድይ፣ የደጅአዝማች በላይ ዘለቀ አየር ማረፊያ አዲስ ተርሚናል፣ የጣና ዳር አረንጓዴ ልማቶች፣ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች እና የኮሪደር ልማትን ለዓብነት አንስተዋል።
“ሀገር ከሁሉም በላይ ናት” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ብልጽግና ሀገርን ከፓርቲ በላይ የማስቀደም ጽኑ መርህ ያለው ፓርቲ ስለመኾኑም ገልጸዋል። በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችም ፓርቲው ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም ሲል አርቆ በማሰብ ያከናወናቸው ናቸው ብለዋል።
በአማራ ክልል የተገነቡ የልማት ሥራዎች የጠላትን ሴራ ከማክሸፍ ጎን ለጎን የተከናወኑ ናቸውም ብለዋል። ልማቶች እንዳይለሙ፣ ይልቁንም ሕዝቡ ወደ ግጭት እንዲገባ ከውጭ ጠላት ጋር እየተባበሩ የሚሠሩ ባንዳዎችን እና የላኪዎቻቸውን ሕልም ማክሸፍ መቻሉ ለተከናወኑ እና ገና ለታለሙ ልማቶች መደላድል ስለመፍጠሩም ተናግረዋል።
አስተዋይ እና አርቆ አሳቢ የኾነው የክልሉ ሕዝብ አሁን ላይ የአጥፊዎችን አካሄድ በውል ተረድቷል ነው ያሉት።
ብልጽግና ፓርቲ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት እና የሥራ ታታሪነት በውል በመረዳት እየሠራ ነው ብለዋል። ሕዝቡ ከገጠሙት ተግዳሮቶች ተሻግሮ ወደ ተሟላ ሰላም እና ልማት እንዲገባ ብልጽግና ፓርቲ ከጎኑ ኾኖ ይሠራል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
