“የኢድ አል ዓደሃ (አረፋ) በዓል የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት በዓል ነው”

11

 

አዲስ አበባ፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 447ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓልን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጫ ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሐመድ ሸሪፍ በዓሉ የነብዩ ኢብራሒም እና የልጃቸው ኢስማኤል ሃይማኖታዊ መስዋዕትነት የሚታወስበት የተከበረ በዓል ነው ብለዋል።

ምዕመኑ አረፋን ሲያከብር በዕለቱ ሶላት ከተሰገደ በኋላ በሚኖረው የእርድ ሥርዓት ሲሶውን ለአቅመ ደካሞች በማካፈል እና እስላማዊ ግዴታውን በመወጣት ሊኾን እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የአሥተዳደር ጉዳዮች እና የተቋማት ልህቀት ምክትል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሼሀቡዲን ሼህ ኑራ የሃይማኖቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ከራስ በላይ ለእህት እና ወንድሞች በማሰብ ሊኾን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በችግር ውስጥ ያሉትን በመደገፍ እና ማኅበራዊ አንድነትን በተግባር በማሳየት ሊኾን እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሃይማኖቱ ተከታዮች ወደ መስገጃ ስፍራ ሲሄዱ እስላማዊ ሥነ ምግባርን እንዲተገብሩ እና በጋራ የሚከበር በዓል እንደመኾኑ በሰላም እንዲከበር ሁሉም አካል ንቁ የሰላም ዘብ ሊኾን ይገባል ብለዋል።

1 ሺህ 447ኛው የኢድ አል ዓደሃ (አረፋ) በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የበረከት እንዲኾንም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ መሠረት መቅጫ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“የሀገራችን ዕድገት እና ልማት ባለቤቶች እኛ በመኾናችን የእኛን ምርጫ ማንም አይመርጥልንም” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
Next article“ባሕር ዳር ከተማ ዐይን ገላጭ ፕሮጀክቶች የተሠሩላት በብልጽግና ፓርቲ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ