
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ እጩዎች፣ ደጋፊዎች እና አባላት የምረጡኝ ቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የክልል ምክር ቤት ዕጩ እና የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ብልጽግና ፓርቲ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሞች እንዲከበሩ አበክሮ እየሠራ ነው ብለዋል።
ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ታላላቅ ብሔራዊ ጥቅሞች እንዲከበሩ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ ማድረግ ችሏል ነው ያሉት። ለዚህም ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ወይም የፖለቲካ ፍላጎት ሳይኾን የሕዝብ የህልውና ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።
የባሕር በር እና የወደብ ጥያቄ በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ለማግኘት ብልጽግና ፓርቲ በትኩረት እየሠራ ነው፤ ቀጣይም ይሠራል ብለዋል።
ፓርቲው በሀገር ሉዓላዊነት እና በብሔራዊ ጥቅሞች አይደራደርም ነው ያሉት።
“የባሕር በር የብልጽግና ፓርቲ ቁልፍ አጀንዳ በመኾኑ ይህን ብሔራዊ ጥቅም እና የትውልድ ጥያቄ ዕውን ለማድረግ መላው ሕዝብ ከጎናችን ሊቆም ይገባል” ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
