
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት በማድረግ ምርጫን የተመለከቱ መረጃዎችን በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በዘገባዎች እና በፕሮግራሞች ለሕዝብ ሲያደርስ ቆይቷል።
የተለያዩ ምርጫን የተመለከቱ መረጃዎችን በማጋራት ከአሚኮ ጋር ሲሠሩ ከነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ብልጽግና፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ይጠቀሳሉ።
አሚኮ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነበረውን ሚና አስመልክተው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ሀሳብ የሰጡት መስፍን አበጀ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለውን አዲስ የፖለቲካ ባሕል ለማጎልበት እና በሀሳብ ብልጫ አሸናፊ የኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብን እና ሀገርን እንዲመሩ ለማድረግ መረጃን ወደ ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ አሚኮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ተናግረዋል።
አሚኮ እንደ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲ የፖሊሲ ሀሳቦችን እና መልዕክቶቹን በአግባቡ ለሕዝብ እንዲያደርስ ያደረገ ሚዲያ እንደኾነ ተናግረዋል። የኅብረተሰቡን ንቃት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረውም አንስተዋል። ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው ያመላከቱት።
ኢዜማ ፓርቲን ወክለው ሀሳብ የሰጡት አቶ ይበልጣል አድማሴ ቀደም ሲል ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ክርክሮችን በአሚኮ አማካኝነት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ባልተሄደበት መንገድ ሚዲያው ደግፎናል ለዚህም ምሥጋና ይገባዋል ብለዋል። አራተኛ መንግሥት የሚባለውን አስተዋጽኦውንም በተግባር እንዳከናወነ ጠቅሰዋል።
የአዴኃን የፖለቲካ ፓርቲን ወክለው የተናገሩት አቶ ይኼነው መስፍን ፓርቲው ከዚህ በፊት ሲያደርጋቸው በነበሩ ክርክሮች እና የዘገባ ሽፋኖች ላይ አሚኮ ለነበረው አስተዋጽኦ ዕውቅና ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዋል። ከዚህ በፊት ባልተለመደ ኹኔታ ሚዲያው ብዙ ተግባራትን ሲፈጽም መቆየቱንም ገልጸዋል። አሚኮ የፓርቲው ሀሳቦች እና መልዕክቶችን ለማኅበረሰቡ በአግባቡ ለማድረስ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማድረጉንም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ባሕል ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስገባት የሚቻልበት አንዱ መንገድ የሕዝብ ሥልጣን ማረጋገጫ የኾነው ምርጫ መኾኑን ነው የተናገሩት። ለዚህም አዴኃን ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ የምርጫ ሀሳብ እና መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ እንደነበር ጠቅሰዋል። ሚዲያው ለነበረው ሚናም ምሥጋና አቅርበዋል።
የአብን ፓርቲን ወክለው ሀሳብ ያጋሩን አቶ መልካሙ ጸጋየ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አሚኮ እንደ ሌሎች ሚዲያዎች ሁሉ ምርጫን አንድ የዘገባ አካል አድርጎ በርካታ ዘገባዎችን ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መረጃ በመውሰድ እና ለሕዝብ በማሠራጨት ዕኩል እንድንሳተፍ አድርጓል ብለዋል። መራጩ ሕዝብ በአሚኮ በኩል አማራጭ ሀሳቦች እንዲደርሱት ሰፊ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል።
የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ክርክር ጨምሮ በሌሎች ዘገባዎች አሚኮ እኩል ዕድል በመስጠት በርካታ የፖሊሲ አማራጮችን እና ሀሳቦችን ማንሳት እንድንችል ምቹ ኹኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት። ይህም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ተጠቃሚ አድርጎናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ጠቅላላ_ምርጫ #ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
